ሕዝቅኤል 33 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሕዝቅኤል የእስራኤል ዘብ 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድሪቱ ሕዝብ ከመካከላቸው አንድ ሰው ወስደው ለራሳቸው ዘበኛ ያደርጉታል፤ 3 እርሱም በምድሪቷ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥ 4 የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። 5 የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር። 6 ዘበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከቱን ባይነፋ፥ ሕዝቡን ባያስጠነቅቅ፥ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእነርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከዘበኛው እጅ እፈልጋለሁ። 7 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ዘበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 8 ኃጢአተኛውን ሰው፦ ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ በምለው ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ባታስጠነቅቀው ያ ኃጢአተኛ ሰው በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 9 ነገር ግን ከመንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን ሰው ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። የእግዚአብሔር ፍትሕና ምሕረት 10 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት፦ እናንተ፦ በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ በእነርሱም እየመነመንን ነው፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። 11 በሕያውነቴ እምላለሁ ኃጢአተኛው ሰው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ኃጢአተኛው እንዲሞት አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። 12 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። 13 እኔ ጻድቁን፦ በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁት ጊዜ፥ እርሱ ጽድቁን ተማምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአትም ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። 14 እኔም ኃጢአተኛውን ሰው፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ 15 ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ፥ የነጠቀውንም ቢመልስ፥ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 16 የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 17 የሕዝብህም ልጆች፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። 18 ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ በእነርሱ ይሞታል። 19 ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በእነርሱ በሕይወት ይኖርበታል። 20 እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ። የኢየሩሳሌም ውድቀት 21 እንዲህም ሆነ፥ በተማረክን በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፦ ከተማይቱ ተመታች አለኝ። 22 ያመለጠው ሰው ከመምጣቱ በፊት በነበረው ምሽት የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ ከዚያም በኋላ ዲዳ አልሆንሁም። በይሁዳ ውስጥ የተረፉት 23 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24 የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ ፍርስራሽ ስፍራዎች የሚኖሩ፦ አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ደግሞ ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። 25 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 26 ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ ሁሉም ወንድ የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአል፤ ታዲያ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 27 እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በፍርስራሽ ስፍራዎች ያሉት በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በሜዳ ያሉትን መብል እንዲሆን ለአራዊት እሰጠዋለሁ፥ በምሽጎችና በዋሻዎች ያሉት በቸነፈር ይሞታሉ። 28 ምድሪቱን ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ። 29 በሰሩትም ርኩሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ በማደርግበት ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 30 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤቶቻቸው ደጃፍ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ አንዱ ከአንዱ ጋር፥ እያንዳንዱ ከወንድሙ ጋር እንዲህ ይላሉ፦ ኑ ከጌታ የመጣው ቃል ምን እንደሆነ እንስማ። 31 ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ያልተገባ ጥቅማቸውን ይከተላልና። 32 እነሆ አንተ እንደ ጥሩ ዘፈን፥ እንደ መልካም ድምፅ፥ እንደ ጎበዝ ተጫዋች ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። 33 ይህም በመጣም ጊዜ፥ እነሆ ይመጣል! ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ። |