Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን ጥበብን ለማግኘት የጸለየው ጸሎት 1 በፍጹም ልቤም እንዲህ አልሁ፥ “የአባቶች አምላክ፥ የምሕረት ጌታ፥ በቃልህ ዓለሙን ሁሉ የፈጠርኽ፤ 2 በጥበብህም ሰውን በአንተ የተፈጠረውን ፍጥረት እንዲገዛ፥ 3 ዓለሙንም በቸርነትና በጽድቅ እንዲሠራራ፥ በቅን ልቡናም እንዲፈርድ ያደረግኸው፥ 4 በዙፋንህ የምትቀመጥ ጥበብን ስጠኝ፥ ከባሮችህም ለይተህ አትናቀኝ። 5 እኔ ባሪያህና የሴት ባሪያህ ልጅ፥ ኀይሌ የደከመ ሰው፥ ዘመኔም ያነሰ፥ ሕግንና ፍርድንም ለማወቅ አነስተኛ ነኝና። 6 “ከሰው ልጆችም ፍጹም የሆነ ሰው ቢኖር፥ በአንተ ዘንድም የምትገኝ ጥበብ ከእርሱ ብትርቅ እርሱ እንደ ኢምንት በሆነ ነበር። 7 አንተ ለሕዝብህ ንጉሥ፥ ለወንዶች ልጆችህና ለሴቶች ልጆችህም ገዢ አድርገህ መረጥኸኝ። 8 በቅዱስ ተራራህ ላይ ቤተ መቅደስ፥ በማረፊያህም ሀገር ከጥንት ጀምሮ ባዘጋጀኸው በቅድስናህ ማደሪያ አምሳል መሠዊያ እንዲሠራ አዘዝኽ። 9 ሥራህንም የምታውቅ ጥበብ ከአንተ ጋር ነበረች፤ ዓለምንም በፈጠርኽ ጊዜ ነበረች፤ በፊትህ ደስ የሚያሰኝህም ምን እንደ ሆነ፥ ለትእዛዝህም የቀናው ምን እንደ ሆነ ትረዳ ነበር። 10 ተነሥታ ትመጣ ዘንድ ከከበሩ ሰማዮች ከጌትነትህ ዙፋን ወደኔ ላካት፤ ከእኔም ጋራ ትኖርና ትደክም ዘንድ ደስ የሚያሰኝህም ምን እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ ላካት። 11 አንተ የምታውቀውን ሥራ ሁሉ ታውቃለችና ንጹሕ አድርጋ ወደ ሥራዎች ሁሉ ትምራኝ፤ በኀይሏም ትጠብቀኝ። 12 ሥራዬ ሁሉ የተወደደ ይሁን፤ ወገኖችህንም በእውነት ልግዛ፤ ለአባቶች ዙፋኖችም የተዘጋጀሁ ልሁን። 13 “የእግዚአብሔርን ምክር የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እግዚአብሔር የሚወድደውንስ ዐስቦ የሚያውቅ ማን ነው? 14 የሟቾች ዐሳባቸው ፈራሽ ነውና፥ የእኛም ዐሳብ ጐፃጕፅ ነውና። 15 የሚፈርስ ሥጋ ነፍስን ያሸንፋታልና፥ ይከብዳታልምና፥ ምድራዊ ማደሪያም ልብን ይሸፍናልና። 16 በብዙ ትጋትና ግዳጅ፥ በጭንቅም ብንመረምር በምድር የሚሠራውን ሥራ እናገኛለን፤ በእጃችን የምንዳስሰውንም ሥራ በድካም እናገኛለን። በሰማይ ያለውን ግን ማን መረመረው? 17 አንተ ጥበብን የሰጠኸው፥ ቅዱስ መንፈስህንም ወደ እርሱ ከላይ የላክህለት ሰው ካልሆነ በቀር ምክርህን ማን ዐወቀ? 18 ስለዚህ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች መንገዳቸው ቀናላቸው፥ ደስ የሚያሰኝህንም ነገር ሰዎች ዐወቁ፥ በጥበብም ዳኑ።” |