Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን ለጥበብ የነበረው ፍቅር 1 ጥበብ ከዳርቻ እስከ ዳርቻ ድረስ ደኅና ሆና ትደርሳለች፤ በቸርነትዋም ሁሉን ትሠራለች። 2 እኔም ከጐልማሳነቴ ጀምሮ ወደድኋት፤ ፈለግኋትም። ለእኔም ሙሽራ አድርጌ እወስዳት ዘንድ ወደድሁ። ደም ግባትዋንም ወደድሁ። 3 የዝምድናዋም ቸርነት ወደ እግዚአብሔር ያቀርባልና ሁሉን የሚገዛ እርሱ ወደዳት። 4 የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለማወቅ መካር ናትና፥ የሥራውም ወዳጅ ናትና። 5 እርሷም ባለችበት ዘንድ ብልጽግና አለ፤ በዚህ ዓለም ገንዘብ ላደረጓት ሰዎች ከሁሉ ትመረጣለች፤ ሁሉን የምታደርግ ጥበብን የሚበልጣት ምንድን ነው? 6 ዕውቀትም ቢደረግ በእርሷ ነው፤ ካሉትም ሁሉ ከእርሷ የሚበልጥ ብልህ ማን ነው? 7 እውነትን የወደደ ሰውም ቢኖር በእርሷ ነው፤ ድካሟ ያማረ ነውና፥ ንጽሕናንና ጥበብን፥ እውነትንና ብርታትን፥ ትሩፋትንና ደግነትንም ታስተምራለች። በዓለሙ ውስጥም በሰው ሕይወት ከእርሷ የሚሻልና የሚጠቅም ምንም የለም። 8 ብዙ ዕውቀትንና ደግነትን ያወቀ ሰው ቢኖር በእርሷ ነው፤ የቀደመውንና የሚመጣውንም ሥራ ያወቀ ሰው ቢኖር በእርሷ ነው፤ የነገር መልስንና ፈጥኖ መተርጐምን ቢያውቅም በእርሷ ነው፤ ተአምራትንና ድንቆችን፥ የጊዜያትንና የዓመታትንም መለዋወጥ አስቀድሞ ቢያውቅ በእርስዋ ነው። 9 እኔም፦ ለበጎ ነገር የምትመክርና የምትገሥጽ ኀዘንንና ትካዝን የምታስተው እንደምትሆን ዐውቄ ከእኔ ጋራ እንድትኖር እይዛት ዘንድ ወደድሁ። 10 በእርስዋም ምክንያት እኔ ጐልማሳው በብዙዎች ዘንድ ምስጋናን፥ በሽማግሌዎችም ዘንድ ክብርን አገኘሁ። 11 ለመፍረድ አሳበ ፈጣን ሆንሁ፤ በኀያላኑም ፊት ተደነቅሁ። 12 ዝም ስልም ታግሠው ይጠብቁኝ ነበር፤ ስናገርም ያዳምጡኝ ነበር፤ መናገርም ባበዛ አፋቸውን በእጃቸው ይይዙ ነበር። 13 በእርስዋም ምክንያት አለመሞትን አገኘሁ፤ ከእኔም በኋላ ለሚመጡ ሰዎች ለዘለዓለም መታሰቢያን ተውሁ። 14 ሕዝቡን እሠራራ ነበር፤ አሕዛብም ይገዙልኝ ነበር። 15 የሚያስደነግጡ የምድር መኳንንትም ሰምተው ይፈሩኝ ነበር፤ በሸንጎ ደግ ሆኜ፥ በጠብም ጊዜ ብርቱ ሆኜ እታይ ነበር። 16 ከእርሷ ጋር መኖር መራራነት የለበትምና፥ ከደስታና ከሐሤትም በቀር ድካምና ኀዘን አይቀርብምና ወደ ቤቴ በገባሁ ጊዜ በእርሷ ዐርፋለሁ። 17 ይህንም በራሴ ሳስብ ኖርሁ፤ ከኀጢአትም መንጻት እንደማይቻለኝ ዐውቄ በልቡናዬ በእርስዋ እተጋለሁ፤ የጥበብ ዝምድናዋ ሕያውነት ነውና። 18 በፍቅሯም መልካም ደስታ አለ፤ በእጅዋ ሥራም የማያልቅ ብልጽግና አለ፤ በነገሯም ውስጥ የዕውቀት ትምህርት አለ፤ ከእርሷም ጋር አንድ በመሆን የሚያስመካ ነገር አለ፤ ለራሴም እወስዳት ዘንድ እየፈለግኋት ሀገሩን ዞርሁ። 19 እኔ ዐዋቂ ልጅ ነኝ፤ ሰውነቴም በጎ ሆነችልኝ። 20 ደግ ነኝና ወደ ንጹሕ ሥጋዋ ገባሁ። 21 እግዚአብሔር እርሷን ካልሰጠኝ በቀር እንደማላገኛት በዐወቅሁ ጊዜ ይህ ምክር ከጥበብ ሆነ፤ የማን ስጦታም እንደ ሆነች ዐውቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፥ ለመንሁትም። |