Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰው ሁሉ መዋቲ ስለ መሆኑ 1 እኔም እንደ ሁሉ እኩል መዋቲ ሰው ነኝ፤ አስቀድሞ የተፈጠረ የምድራዊ አዳም ልጅም ነኝ፥ በእናቴ ማኅፀንም ሥጋ ሆኜ ተቀርጫለሁ። 2 በመገናኘት ጊዜ ከአባት ዘርና ከመኝታ ፈቃድ ተገኝቼ፥ ዐሥር ወር በደምነት ረግቼ ኖርሁ። 3 በተፈጠርሁም ጊዜ እንደ ሰው ሁሉ ነፍስን ነሣሁ፥ በመከራዬም ምሳሌ ወደ ምድር ወረድሁ፤ የቃልም መጀመርያ እንደ ሁሉ ልቅሶን አለቀስሁ። 4 በጨርቅ ተጠቅልዬ በጥንቃቄ አደግሁ። 5 ከነገሥታት ወገን የልደቱ መጀመሪያ ልዩ የሆነ የለምና። 6 የሁሉም ወደዚህ ዓለም አመጣጡ አንዲት ናት፥ የሁሉም መውጣቱ እኩል ነው። ሰሎሞን ለጥበብ የነበረው ፍቅር 7 ስለዚህ ነገር ጸለይሁ፤ ዕውቀትም ተሰጠኝ፤ ለመንሁ፤ የጥበብም መንፈስ ወደ እኔ መጣ። 8 ከበትረ መንግሥትና ከዙፋንም ይልቅ አከበርኋት፤ ብዕልንም ከእርስዋ ጋር ሳመዛዝን እንደ ኢምንት አደረግኋት። 9 ወርቅ ሁሉ በእርሷ ዘንድ እንደ ጥቂት አሸዋ ነውና፤ ብሩም በእርስዋ ዘንድ እንደ ጭቃ ነውና፥ ዋጋ በሌለው ዕንቍ አልመሰልኋትም። 10 ከሕይወትና ከውበትም ፈጽሜ ወደድኋት፤ ከእርሷ የሚወጣ የብርሃን ነጸብራቅ አይወሰንምና፥ ደግሞም አይጠፋምና ስለ ብርሃን ፋንታ ትሆነኝ ዘንድ መረጥኋት። 11 ከእርሷ ጋር በአንድነት በጎ ነገር ሁሉ መጣልኝ፤ ቍጥር የሌለው ባለጠግነትም በእጆችዋ አለ። 12 ጥበብ የእነዚህ ሁሉ አበጋዛቸው ናትና በሁሉ ደስ አለኝ፤ ጥበብ የእነዚህ ሁሉ አስገኛቸው እንደ ሆነች አላወቅሁም ነበር። 13 ይህን ባወቅሁ ጊዜ ያለ ክፋትና ያለ ቅንአት እርሷን እሰጣለሁ፤ ብልጽግናዋንም አልሰውርም። 14 ለሰውም የማያልቅ መዝገብ ናት፤ ገንዘብ ያደረጓትም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ደረሱ፤ ሀብትን የምትገልጽ የምክር ሥራ ስለ ሆነችም ተወዳጇት። 15 ለእኔም እግዚአብሔር የሚወደደውን ነገር እናገር ዘንድ፥ ለሚሰጠውም ሰው የሚገባውን አስብ ዘንድ ጥበብን ሰጠኝ። ወደ ጥበብ የሚመራ፥ ጠቢባንንም ቅን የሚያደርግ እርሱ ነውና። 16 እኛ ሁላችን በእጁ ነንና፤ ነገራችንም ሁሉ ሥራችንንም ማወቅና መረዳት በእጁ ነውና። 17 ያለ ሐሰት ነዋሪ የሚሆን የዕውቀት ነገርን ሰጠኝ፤ ዓለም ጸንቶ የሚኖርበትንም ሥርዐት፥ የፀሐይን፥ የጨረቃንና የከዋክብትንም ሥራ አውቅ ዘንድ፤ 18 የዘመኑን መጀመሪያውንና መጨረሻውን፥ መካከሉንም፥ የቀኑን መመላለስ፥ የጊዜውንም መለዋወጥ፥ 19 የዘመናትን ዑደት፥ የከዋክብትንም አኗኗር፥ 20 የእንስሳንም ጠባይ፥ የአራዊትንም ቍጣ፥ የነፋሳትንም ኀይል፥ የሰውንም አሳብ፥ ዛፎችንም ለይቶ ማወቅ፥ የሥሮችንም ተግባር ኀይል አውቅ ዘንድ ሰጠኝ። 21 የሥራው ሁሉ አስገኝ እርሱ ጥበብን አስተምሮኛልና የተገለጸውንና የተሰወረውን ሁሉ ዐወቅሁ። የጥበብ ጠባይ 22 በእርስዋ የማስተዋል መንፈስ አለና፤ እርሱም ቅዱስ፥ በልደት ብቸኛ የሆነ፥ አንድ ሲሆን ሀብቱ ብዙ የሆነ፥ ረቂቅ፥ እንቅስቃሴውም የፈጠነ፥ ቃሉ የሚያምር፥ ጠቢብ፥ ዕድፈትም የሌለበት፥ የማይደክም፥ ጥንት የሌለው፥ ነዋሪ፥ ቸርነትን የሚወድ፥ ፈጣን፥ በጎ ነገርን ለማድረግ የሚከለክለው የሌለ፥ 23 ሰው ወዳጅ፥ የጥበብ ወዳጅዋ፥ ዐዋቂ፥ እውነተኛ፥ ግዳጅ የሌለበት፥ ትዕግሥተኛ፥ ሁሉን የሚችል፥ ሁሉንም የሚጐበኝ፥ ንጹሓትና አስተዋዮች፥ ረቂቃትም በሆኑ ነፍሳት የሚያድር ነው። 24 የጥበብ እንቅስቃሴዋ ከእንቅስቃሴ ሁሉ ይፈጥናልና። በሁሉም ዘንድ በስፋት ትመላለሳለች፤ ስለ ንጽሕናዋም ጽርየት በሁሉ ትሄዳለች። 25 የእግዚአብሔር የኀይሉ እስትንፋስ ናትና፥ አርአያው የታወቀ፥ ክቡርና ንጹሕ የሆነ የኀያል አምላክ የክብሩ መገለጫ ናት። ስለዚህ የሚያገኛት ምንም ርኵሰት የለም። 26 የቀዳማዊ ብርሃን ነጸብራቅ ናትና፥ የማትጨልም የእግዚአብሔር የሥራው መስታዋትም ናትና፥ የቸርነቱም አርኣያ ናትና። 27 አንዲት ስትሆን ሁሉን ማድረግ ትችላለች፤ ራስዋም እየኖረች ሁሉን ታድሳለች፥ በየትውልዱም በጻድቃን ሰውነት ትተላለፋለች፤ የእግዚአብሔርም ወዳጆችና ነቢያቱ ታደርጋቸዋለች። 28 እግዚአብሔር ከጥበብ ጋር ከሚኖር ሰው በቀር የሚወድደው የለምና። 29 እርስዋ ከፀሐይ ይልቅ በመልክ ታምራለችና፥ ከከዋክብትም ሥርዐት ሁሉ ትበልጣለች፤ ከብርሃን ጋርም በምትመዘንበት ጊዜ በልጣ በፊቱ ትገኛለች። 30 ብርሃኑን ሌሊት ይለውጠዋልና፥ ጥበብን ግን ምንም ክፉ ነገር አይበረታታባትም። |