Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የገዥዎች ሐላፊነት 1 ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ አስተውሉም፤ የምድር ዳርቻንም የምትገዙ መኳንንት ሆይ፥ ዕወቁ። 2 ብዙ ምድርን የምትገዙ፥ በሠራዊትም ብዛት የምትታበዩ ስሙ። 3 እግዚአብሔር ኀይልን ሰጥትዋችኋልና፤ ግዛታችሁም ከልዑል ዘንድ ነው፤ ምግባራችሁንም የሚመረምር እርሱ ነው፤ ምክራችሁንም ይመረምራል። 4 እናንተ የመንግሥቱ መልእክተኞች ስትሆኑ የቀና ፍርድን እንዴት አትፈርዱም? ሕጉንስ እንዴት አልጠበቃችሁም? በእግዚአብሔርስ መንገድ እንዴት አልሄዳችሁም? 5 ፈጥኖ የሚቃወማችሁ ድንጋፄን በላያችሁ ያመጣል፥ ቍርጥ ፍርድ በመኳንንት ላይ ይሆናልና። 6 ለተዋረደው ድሃ ግን ከቸርነት ሥራ የተነሣ ይቀልለታል፤ ኀይለኞች ሰዎች ግን በጽኑዕ ምርመራ ይመረመራሉ። 7 እግዚአብሔር ፊት አይቶ አያዳላምና፤ የታላቁንም መከበር አያፍርምና፤ እንደዚሁም ታናሹንና ታላቁን ስለ ፈጠረ ለገዡና ለተገዡ ሁሉ ያስባል፤ ይወስንላቸዋልም። 8 በኀያላን ግን ጽኑዕ ምርመራ ይደርስባቸዋል። 9 ክፉዎችና ግፈኞች መኳንንት ሆይ፥ ጥበብን እንድታውቁና እንዳትሰነካከሉ ነገሬ ለእናንተ ነው። 10 እውነተኛ ትእዛዙን ዐውቀው የሚጠብቁ በእውነት ይከብራሉና የተማሯትም ሰዎች ምሕረትን ያገኛሉና። 11 እንግዲህ ወዲህ ነገሬን ተመኝዋት፥ ውደዷትም፤ ይቅርታንና ቸርነትንም ታገኙ ዘንድ ተመከሩ። የጥበብ ዋጋ 12 ጥበብ ፈጽማ የጐላች ናት፤ ውበቷም አይጠወልግም፤ የሚወድዷትም ሰዎች ፈጥነው ያዩአታል፥ የሚፈልጉአትም ያገኙአታል። 13 ለሚወዷትም ትደርስላቸዋለች፤ አስቀድማም ትገለጥላቸዋለች። 14 በደጃፉ ስትጠብቀው ሁል ጊዜ እርሱ ያገኛታልና ወደርስዋ የሚገሠግሥ ሰው አይደክምም። 15 እርስዋን ማሰብ የዕውቀት ፍጻሜ ነውና፥ ፈጥኖ ስለ እርስዋ የሚተጋ ሰው ያለ ኀዘን ይኖራል። 16 ለእርስዋ የሚገቧትን ሰዎች ፈልጋ ትመጣለችና፥ በመንገድም ድንገት እንደ ሥዕል አምራ ትታያቸዋለች፤ በአሳብም ሁሉ ትገናኛቸዋለች። 17 የጥበብ መጀመሪያ ተግሣጽን መውደድ ነው፤ ተግሣጽንም ማሰብ እርሷን መውደድ ነው። 18 እርሷንም መውደድ ሕጓን መጠበቅ ነው፤ ሕጓንም መስማት ሕይወትን መረዳት ነው። 19 ሕይወትም ሰውን ወደ እግዚአብሔር የቀረበ ታደርጋለች። 20 ጥበብን መውደድ ወደ መንግሥት ታደርሳለችና። 21 የአሕዛብ ነገሥታት ሆይ፥ ዙፋንንና በትረ መንግሥትን ከወደዳችሁ ለዘለዓለም ትነግሡ ዘንድ ጥበብን አክብሯት። 22 ጥበብ ምንድን ናት? እንደ ምንስ ነበረች? እኔ እነግራችኋለሁ፤ የተሰወረ ምሥጢሯንም ከእናንተ አልሰውርም። ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ አኳኋኗን እመረምራለሁ፤ እርሷን ማወቅንም የተገለጠ አደርጋለሁ፤ እውነትንም አልተላለፍም። 23 በምቀኛ ቅንአት አልኖርም፤ እንዲህ ያለ ሰው ከጥበብ ጋራ አንድ አይሆንምና። 24 የጠቢባን ብዛት የዓለም መድኀኒት ነውና። 25 አስተዋይ ንጉሥም ለሕዝቡ ጠበቃ ነው፤ በቃሌም ተመከሩ፤ ትጠቀማላችሁም። |