Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጥፋት የሌለበት ቸር መንፈስህ በሁሉ አለና። 2 ስለዚህም የተሰነካከሉትን ሰዎች ለፍርድ እንዲመች ጥቂት በጥቂት ትዘልፋቸዋለህ፤ የበደሉትንም በደል ታሳስባቸዋለህ፤ ከክፋታቸውም ርቀው ኀጢአታቸውን በተረዱ ጊዜ አቤቱ፥ ያምኑብህ ዘንድ ትገሥጻቸዋለህ። ስለ ከነዓናውያን ኀጢአት 3 በቅድስት ሀገርህ የሚኖሩትን የቀደሙትን ሰዎች፥ 4 ስለ ተጠላ የሟርት ሥራቸውና ከጽድቅ ስለራቀ በዓላቸው፥ 5 ያለርኅራኄም ልጆቻቸውን ስለመግደላቸው፥ የሰዎችን ሆድ ዕቃና ሥጋቸውን ለመብላት፥ ደማቸውንም ለመጠጣት ስለ መፍቀዳቸው ጠልተኻቸዋል። የጌትነትህን ምሥጢራት ማወቅ ከመካከላቸው ርቋልና። 6 ከማንም ዘንድ ረዳት የሌላቸው ሰዎችንም ይገድላሉ፥ በአባቶቻችንም እጅ ታጠፋቸው ዘንድ ወደድህ። 7 ይህም የእግዚአብሔር ልጆች ከሀገሩ ሁሉ በአንተ ዘንድ የከበረች ለእነርሱ የምትገባ ሀገርን ይይዙ ዘንድ ነው። 8 ነገር ግን ሰውን ይቅር እንደምትል እነርሱንም ይቅር አልኻቸው፤ እነርሱንም ጥቂት በጥቂት እንዲያጠፉ ከሠራዊትህ አስቀድሞ የትንኝ ወራሪን ላክህባቸው። 9 ያም ባይሆን በየወገኖቻቸው እንዲማርኳቸው ክፉዎችን በጻድቃን እጅ ትጥላቸው ዘንድ አይሳንህም ነበር፥ ያም ባይሆን ለክፉዎች አውሬዎች ትሰጣቸው ዘንድ፥ ያም ባይሆን በአንድ ቃል አዝዘህ ታጠፋቸው ዘንድ አይሳንህም ነበር። 10 ለእነዚህ የንስሓ ቦታ ሰጥተህ ይህ ጥቂት በጥቂት ይሆን ዘንድ ፈረድህ፤ ይህንም ማድረግህ አኗኗራቸው ክፉ እንደ ሆነ፥ ክፋታቸውም እጅግ እንደ በዛ፥ ዐሳባቸውም ለዘለዓለም እንደማይመለስ ሳታውቅ አይደለም። 11 ከጥንት ጀምሮ የተረገሙ ዘሮች ናቸውና፥ በበደሉበት በደል ዕድሜን የምትሰጣቸው ማንንም አፍረህ አይደለም። እግዚአብሔር የሁሉ ገዥ ስለ መሆኑ 12 “ምን አደረግህ?” የሚልህ ማን ነው? ፍርድህንስ የሚቃወመው ማን ነው? ወይስ የሚከስህ ማን ነው? አንተ የፈጠርኻቸው አሕዛብስ ስለ ጠፉ የሚመራመርህ ማን ነው? ስለ በደለኞች ሰዎችም ለመከራከር ወደ አንተ የሚደርስ ዳኛ ማን ነው? 13 የፈረድህ በግፍ እንዳይደለ ትገልጥ ዘንድ ስለ ሰው ሁሉ የሚያስብ ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለምና። 14 ንጉሥም ቢሆን፥ መስፍንም ቢሆን ስለ ፈረድህባቸው ሰዎች አንተን እያማ ከአንተ ጋር መተያየት አይችልም። 15 አንተ ሁሉን በእውነት የምታዘጋጅ እውነተኛ ነህና ለፍርድ የተገባ ያይደለውን ትፈርድበት ዘንድ ከኀይልህ የተነሣ ልዩ ሥራ ነው። 16 ከሃሊነትህ የጽድቅ መጀመሪያ ነውና፥ ሁሉን መፍጠርህና መግዛትህ ሁሉን ይቅር እንድትል ያደርግሃል። 17 የከሃሊነትህንም ፍጻሜ በማያምን ኀይልህን ገልጠሃልና የማያምኑትን መደፋፈራቸውን ትዘልፋለህ። 18 አንተ ኀያል መኰንን ስትሆን በቅንነት ትፈርዳለህ። መቼም ቢሆን ከወደድህ ከሃሊነት በአንተ ዘንድ አለና በብዙ ቸርነት ታኖረናለህ። 19 እንዲህ ባለ ሥራም ጻድቅ ሰው ርኅሩኅና ሰው ወዳጅ መሆን ይገባው ዘንድ ወገኖችህን አስተማርህ፤ ለልጆችህም በጎ ተስፋን አደረግህ፥ አንተ ለበደለኛ ንስሓን ትሰጣለህና። 20 ለሞት የሚገቡ እነዚህ የልጆችህ ጠላቶች ባሉበት ዘንድም በእንዲህ ያለ ትዕግሥት ፈረድህ፥ ከክፉም ይድኑባት ዘንድ ዘመንንና መንገድን ሰጠሃቸው። 21 ለበጎ ተስፋ መሓላንና ቃል ኪዳንን ለሰጠሃቸው ለልጆችህ ምን ያህል ተጠንቅቀህ ትፈርድላቸው ይሆን? 22 ስለዚህም በፈረድህባቸው ጊዜ ቸርነትህን እናስብ ዘንድ፥ እኛን እየመከርህ ጠላቶቻችንን በብዙ ፍርድ ብዙ ጊዜ ትቀጣቸዋለህ፤ በፈረድህብንም ጊዜ ይቅርህታን ተስፋ እናደርጋለን። ስለ ግብፃውያን ቅጣት 23 በዚህ ግን በስንፍናና በኀጢአት የኖሩ በደለኞች ሰዎችን ቀጣህ፥ በየራሳቸውም ኀጢአት ፈረድህባቸው። 24 በጠላቶቻቸው ዘንድ ያሉ የተዋረዱ ከብቶችን አማልክት እያሉ ብዙ ዘመን በስሕተት ጐዳና ተጐድተዋልና፥ ዕውቀት እንደሌላቸው ልጆችም ሐሰትን ተናገሩ። 25 ስለዚህም ምክንያት እንደሌላቸው ሕፃናት ስለሆኑ እንደ ዋዛቸው መጠን ፍርድን በእነርሱ ላይ አመጣህ። 26 በቍጣው ተግሣጽ ካልተመለሱ የጻድቅ እግዚአብሔር የፍርዱን እንጀራ ይቅመሱ፤ እነርሱ ባገኛቸው መከራ አንጐራጕረዋልና፥ ቸልም ብለዋልና። 27 አማልክት እንደ ሆኑ ባሰቧቸው በእነዚህ በጣዖታቱ በተፈረደባቸው ጊዜ ቀድሞ የካዱትን ያውቁታል፥ ጻድቅ አምላክ እንደ ሆነም ያውቁታል፤ ስለዚህም ፍጹም የፍርድ ቅጣት ደረሰባቸው። |