Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጥበብ ሰውን እንደምትጠብቅ 1 ይህቺ አስቀድሞ የተፈጠረ የዓለምን አባት ጠበቀች፥ ብቻውንም ከተፈጠረ በኋላ እንደ አደራ ጠበቀችው፥ ከራሱ በደልም አዳነችው። 2 ሁሉንም ይገዛና ይይዝ ዘንድ ኀይልን ሰጠችው ። 3 በደለኛና ግፈኛ ሰውም በቍጣው ከእርሷ በራቀ ጊዜ፥ ወንድሞቻቸውን ከሚገድሉ ሰዎች ጋር በመዓት ጠፋ። 4 ዳግመኛም ምድር በማየ አይኅ በጠፋች ጊዜ ጥበብ ጻድቁን አዳነችው፥ በተናቀ እንጨት ዕቃም አሻገረችው። 5 አሕዛብ ወደ ተለያየ ክፋትና ጥመት ተጨልጠው በሄዱ ጊዜ ጻድቁን አመለከተችው፤ ያለ በደልና ያለ ነውር ለእግዚአብሔር ጠበቀችው፤ በቸርነትም የጸና ልጁን ጠበቀች። 6 ይህቺ ከሚጠፉ ዝንጉዎች ሰዎች ለይታ ጻድቁን ልጅ አዳነች፥ በአምስቱ ከተሞችም ላይ እሳት በወረደች ጊዜ በመሸሽ አዳነችው። 7 ለክፋታቸው ምስክር ልትሆን እስከ ዛሬ ድረስ ምድረ በዳ ሆና እየጤሰች አለች፥ ተክሎችዋም በጊዜዋ ቢያፈሩ ፍጹማን ያልሆኑ ናቸው፤ ያላመነች ሰውነትም መታሰቢያ ሆኖ የሚታይ የጨው ድንጋይ ሆና ቆማለች። 8 እነዚህ ጥበብን የተላለፉ ናቸውና ደግ ነገርን ባለማወቅ የደረሰባቸውን መዓት በማወቅ እንደ እነዚያ የጠፉ ብቻ አይደለም። ነገር ግን የበደሉትን በደል መሰወር እንዳልተቻላቸው መጠን ለስንፍናቸው መታሰቢያን በዚህ ዓለም ተዉ። 9 ጥበብስ የሚያገለግሏትን ሰዎች ከድካምና ከመከራ አዳነች። 10 ይህች ከወንድሙ ቍጣ የተነሣ የሸሸውን ጻድቅ ሰው ወደ ቀና መንገድ መራችው። የእግዚአብሔርንም መንግሥት አሳየችው፤ የተቀደሱትንም ማወቅን ሰጠችው፥ ከድካሙ የተነሣም አበለጸገችው፥ ጥሪቱንም አበዛችለት። 11 ከሚቀሙትና ከሚበረታቱበትም ሰዎች የተነሣ ጠበቃ ሆና ቆመችለት፤ ረዳችውም። 12 ከጠላቶቹም እንደ አደራ ዕቃ ጠበቀችው፥ ከከበቡትም ሰዎች አዳነችው። ለእግዚአብሔርም በበጎ መገዛት ከሁሉ እንደሚጸና ያውቅ ዘንድ በጽኑ ገድል ጊዜ ድልን ሰጠችው። 13 ይሀቺ ጥበብ በተሸጠ ጊዜ ጻድቁን ሰው አልተለየችውም፤ ነገር ግን ወደ ጕድጓድ ከእርሱ ጋር ወረደች፥ ከኀጢአትም አዳነችው። 14 በተበረታቱበትም ሰዎች ላይ ግዛትንና የመንግሥትን ሹመት እስከምታመጣለት ድረስ በታሠረበት አልተለየችውም። የናቁትንና ያነወሩትንም ሐሰታቸውን ገለጠችባቸው። የዘለዓለምንም ክብር ሰጠችው። ጥበብ እስራኤልን ከግብፅ መርታ እንዳወጣቻቸው 15 ይህቺም ጥበብ ጻድቅ ሕዝብን፥ ነቀፋ የሌለበት ዘርንም ከሚያስጨንቋቸው አሕዛብ አዳነች። 16 በእግዚአብሔር ባሪያ ሰውነትም አደረች፤ በተአምራትና በድንቅ ሥራዎችም የሚያስደነግጡ ነገሥታትን ተቃወመች። 17 ለቅዱሳንም የድካማቸውን ዋጋ ሰጠቻቸው፥ የተደነቀ መንገድንም መራቻቸው፥ በቀንም ጥላ ሆነቻቸው፥ በሌሊትም ስለ ከዋክብት ብርሃን ፈንታ ብርሃን ሆና አበራችላቸው። 18 የሚያስፈራ የኤርትራ ባሕርንም አሻገረቻቸው፥ በብዙ ውኃ መካከልም አሳለፈቻቸው። 19 ጠላቶቻቸውን ግን አሰጠመች፥ እነርሱንም ከጥልቅ ባሕር አወጣቻቸው። 20 ስለዚህም ነገር ጻድቃን ክፉዎችን ማረኩ። አቤቱ ቅዱስ ስምህንም አመሰገኑ። ተዋጊና አሸናፊ እጅህንም በአንድነት አከበሩ። 21 ጥበብ የዲዳዎችን አፍ ከፍታለችና፥ የሕፃናትንም አንደበት ቀንቶ የሚናገር አድርጋለችና። |