Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ሲራክ 41 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ሞት 1 ሞት ሆይ፥ ሰው በደኅና ሲኖር፥ በሁሉ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ኀይልም ሳለው፥ ለመብላትም ሆዱ ተከፍቶ ሳለ፥ በሰው ላይ በምትመጣ ጊዜ ስም አጠራርህ እንዴት መራራ ነው! 2 ሞት ሆይ፥ ኀይል በሌለው፥ ፈጽሞም ባረጀ፥ ሊያደርገውም የሚችል ምንም በሌለው፥ የሚያውቀውም በሌለው፥ በድሃ ሰው ላይ በምትመጣ ጊዜ ፍርድህ እንዴት መልካም ነው! 3 የሞትን ፍርድ አትፍራ፤ ከአንተም በፊት የነበሩትንና ከአንተም በኋላ የሚነሡትን አስባቸው። የእግዚአብሔር ፍርድ በሰው ሁሉ ላይ ነው፤ 4 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለምን ትነቅፋለህ? ዐሥር ዓመት፥ መቶ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም በሕይወት ብትኖር፥ ከሞት ጋራ ክርክር የለህም። 5 የኀጢአተኞች ሰዎች ልጆች ጐስቋሎች ልጆች ይሆናሉ፤ የክፉዎች ሰዎችም ቤታቸው ይፈርሳል። 6 የኀጢአተኞች ልጆች ርስታቸውን ያጣሉ፤ ኀጢአታቸውም ከዘራቸው ጋር አደገ። 7 ስለ እርሱ ይዋረዳሉና፥ የኀጢአተኛ አባት ልጆች ይጐሰቍላሉ። 8 የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ ላፈረሳችሁ ኀጢአተኞች ሰዎች ወዮላችሁ! 9 ብትወልዱም ለርግማን ትወልዳላቸሁ፤ ብትሞቱም ዕድል ፋንታችሁ ርግማን ነው። 10 ሁሉ ከምድር ተፈጠረ፤ መመለሻውም ወደ ምድር ነው፤ ኀጢአተኞችም እንዲሁ ከርግማን ወደ ጥፋት ይሄዳሉ። 11 የሰው ኀዘኑ ስለ ሰውነቱ ነው፤ የኀጢአተኞችም ስማቸው ይደመሰሳል። 12 መልካም ስምን ታስጠራ ዘንድ አስብ፤ ከሺህ ታላላቅ የወርቅ መዛግብትም እርሱ ብቻ ይቀርሃል። 13 በዘመንህ ቍጥር በደስታ መኖር መልካም ነው፤ እርሱ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖርልሃልና መልካም ስም ይሻላል። 14 ጥበብ ግን ልጆችዋን በሰላም ትጠብቃቸዋለች፤ የተሰወረ ጥበብና የማይታይ ድልብ፥ የሁለቱ ጥቅማቸው ምንድን ነው? 15 ጥበቡን ከሚሰውር ሰው፤ ስንፍናውን የሚሰውር ሰው ይሻላል። 16 እንግዲህ ቃሌንና ጥበቤን እፈሩ፤ የሚያፍር ሁሉ በበጎ ይጠበቃል፤ በሁሉ ይማከር ዘንድ ሁሉ የታመነ አይደለም። 17 ልጅ እንወልዳለን ብለው በዝሙት መኖር፤ ለአባትና ለእናት ኀፍረት ነው ለአለቃና ለታላላቆችም መዋሸት ኀፍረት ነው። 18 ለሹምና ለዳኛ ቃል መለወጥ ኀፍረት ነው። ለማኅበርና ለሕዝብም መሳት ኀፍረት ነው፤ ከጓደኛህና ከወዳጅህ ጋር መከዳዳት ኀፍረት ነው። 19 ለእንግዳ በእንግድነት ካደረበት ቤት ሰርቆ መሄድ ኀፍረት ነው፤ የእግዚአብሔርንም እውነትና ቃል ኪዳን ማፍረስ ኀፍረት ነው፤ የሌላ ሰው እህል ለመብላት በመስገብገብ መቅረብ ኀፍረት ነው፤ አደራ ከአስጠበቁህ ገንዝብና ከባልንጀራህ ገንዘብ መስረቅ ኀፍረት ነው። 20 የሚጠራህን ሰው ቸል ማለት ኀፍረት ነው፤ ወደ ሌላ ሰው ሚስትም መመልከት ኀፍረት ነው። 21 በመከራው ጊዜ ባልንጀራህን ቸል ማለት ኀፍረት ነው፤ በሌላ ሰው ገንዘብም መሳሳት ኀፍረት ነው። የጎልማሳ ሚስት ማነጋገርም ኀፍረት ነው። 22 ገረዱንም አታባብላት፤ ወደ መኝታዋም አትቅረብ፤ ወዳጅህን መሳደብ ኀፍረት ነው፤ ከሰጠኸውም በኋላ አትሳደብ፤ የሰማኸውን ነገር ማውጣት፥ መናገርም ኀፍረት ነው። ምሥጢርንም መግለጥ ኀፍረት ነው፤ 23 ይህን ብትጠብቅ በእውነት ኀፊረ ገጽ ያለህ ትሆናለህ፤ በሰውም ሁሉ ዘንድ መወደድን ታገኛለህ። |