Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ሲራክ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በአፉ ያልተሰነካከለ ሰው ብፁዕ ነው፤ ኀጢአተኛ ሰውን ግን ኀዘን አያስደነግጠውም። 2 ሰውነቱን የማያሳዝን፥ ተስፋውንም የማይቈርጥ ሰው ብፁዕ ነው። ሀብትን በሚገባ ስለ መጠቀም 3 ነገርን ለማያውቅ ሰው ብልጽግና አይገባውም፤ ለንፉግም ሰው ገንዘብ አይገባውም። 4 ሰውነቱን የሚነፍጋት ሰው ለሌላ ያከማቻል፥ ሌላ ሰው ግን በገንዘቡ ደስ ይለዋል። 5 ሰውነቱን የሚነፍግ በገንዘቡም ደስ የማይለው ሰው፥ ለማን ይለግስ ዘንድ አለው? 6 ሰውነቱን ከሚነፍግ ሰው የሚከፋ የለም፤ ለክፋቱም እርሱ ፍዳ ይሆነዋል። 7 በጎ ቢያደርግም ባረጀ ጊዜ ብቻ ነው፥ ኋላም ክፋቱን ያሳውቃል። 8 የንፉግ ሰው ዐይኑ ክፉ ነው፥ ከድሃ ፊቱን የሚመልስ ሰውነቱን ቸል ይላል። 9 ለስሱ ሰው ዐይን ድርሻው አያጠግበውም፤ የልቡናውም ክፋት ሰውነቱን ያከሳዋል። 10 የንፉግ ሰው ዐይኑ እህል ይነፍጋል፤ በማዕድም ይነፍጋል። 11 ልጄ ሆይ፥ የሚቻልህን ያህል ሰውነትህን አዘጋጃት፥ እንደሚገባህም ለእግዚአብሔር መባእ አግባ። 12 ሞት እንደማይቀር ዐስብ፥ የምትሞትባትም ቀን ትቀራለች ብለህ አትጠራጠር። 13 ሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ አድርግ፤ እጅህንም ዘርግተህ የተቻለህን ያህል ስጥ። 14 በደስታህ ጊዜ አትታጣ፤ በጎ ድርሻህም አያምልጥህ። 15 ገንዘብህን ለባዕድ የምትተው አይደለምን? ወራሾችህስ ገንዘብህን ሁሉ የሚካፈሉ አይደለምን? 16 ገንዘብህን አንሥተህ ስጥ፥ ሰውነትህንም ደስ አሰኛት፥ በመቃብር የምታገኘው ደስታ የለምና። 17 ሰው ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃል፥ ሞትን ትሞት ዘንድ የሕግ ትእዛዝ ተሠርትዋልና። 18 ቅጠሉ ጭፍቅ ያለ የእንጨት ቅጠል የመጀመሪያው ቅጠል እንዲረግፍ የኋላውም እንዲለመልም፤ ደማዊና ሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ እንዲሁ ነው፤ ይህ ይወለዳል ያም ይሞታል። 19 ሥራ ሁሉ ፈጽሞ ይጠፋል፤ ሠሪውም ከሥራው ጋር ይጠፋል። ጥበብን በመፈለግ የሚገኝ ደስታ 20 ነገር ግን ብልህ ሆኖ የሞተ፥ ጥበቡንም ተምሮ የጠበቀ ሰው ብፁዕ ነው። 21 የጥበብን መንገድ በልቡ የሚያስብ፥ ምሥጢሯንም የሚማር፥ 22 ጥበብን የሚከተላት፥ ፍለጋዋንም የሚመረምር፥ መንገድዋንም የሚጠብቅ፥ 23 መስኮትዋን የሚጎበኝ፥ በበሮችዋም ተቀምጦ የሚያዳምጥ፥ 24 በቤትዋም አጠገብ የሚኖር፥ በዙሪያዋም የድንኳኑን ካስማ የሚተክል፥ 25 ድንኳኑን በአጠገብዋ የሚያቆም፥ ባማረ ማደሪያዋም የሚኖር፥ 26 ልጆቹንም በጥላዎችዋ የሚያስቀምጥ፥ በቅርንጫፎችዋም በታች የሚያድር፥ 27 ከበረሃ ሐሩርም በበታችዋ የሚጠለል፤ በክብርዋም የሚያርፍ ብፁዕ ነው። |