Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ሲራክ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጥበብ መንገዶች 1 የጥበብ ሁሉ መገኛዋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ ለዘለዓለምም ከእርሱ ጋር ናት። 2 የባሕር አሸዋን፥ የዝናም ጠብታን፥ የዘለዓለምነት ቀኖችንስ ማን ቈጠረ? 3 የሰማይን ምጥቀት፥ የምድርን ስፋት፥ የባሕርን ጥልቀት፥ ጥበብንም ማን መርምሮ አገኛቸው? 4 ጥበብ ከሁሉ አስቀድሞ ተፈጠረች። 5 የጥበብ መታሰቧ ከጥንት ጀምሮ ነው። 6 የጥበብ ሥርዋ ለማን ተገለጠ? 7 ምክሯንስ ማን ዐወቀ? 8 ጥበበኛ አንድ ነው፥ እጅግም የሚያስፈራ ነው፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ጸንቶ ይኖራል። 9 እርሱ እግዚአብሔር ሠራት፤ አያት፥ ሰፈራትም። በሥራውም ሁሉ ላይ አሳደራት፤ 10 እርስዋም እንደ እርሱ ስጦታ ከሥጋዊ ሁሉ ጋር ናት፥ ለሚወዱትም ሁሉ እርስዋን ሰጣቸው። 11 እግዚአብሔርን መፍራት ክብር ነው፥ የሚያስመካም ነው፥ ደስታም ነው፥ የደስታ ዘውድም ነው። 12 እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፤ ሐሤትንም ይሰጣል፤ ደስም ያሰኛል፥ የሕይወትንም ዘመን ያረዝማል። 13 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ፍጻሜው ያምራል፤ በሚሞትበትም ቀን ይከብራል። 14 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ በእናታቸው ማኅፀን ከምእመናን ጋር ተፈጠረች። 15 ከሰዎችም ጋር የዓለምን መሠረት ፈጠረች፤ ከዘራቸውም ጋር ልትኖር ታመነች። 16 ጥበብን መጥገብ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ በፍሬዋም ታጠግባቸዋለች። 17 በቤቶችዋም ደስታ መልትዋል፥ በቦታዎችዋም ፍሬ አለ። 18 የጥበብ ዘውድዋ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰላምን ያመጣታል፥ ይፈውሳል፥ ያድናልም። 19 ፈጣሪዋ አያት፥ ሰፈራትም፥ የምክርንና የዕውቀትን የጥበብንም ምንጭ አፈሰሰ፥ የሚያጸኗትንም ሰዎች አገነናቸው፥ አከበራቸውም። 20 የጥበብ ሥር እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ቅርንጫፍዋም የሕይወትን ዘመን ያረዝማል። ከኀጢአት ለመራቅ ራስን መቈጣጠር 21 በተቈጣ ጊዜ መከራ ይመጣበታልና ቍጡና ዐመፀኛ ሰው መጽደቅ አይችልም። 22 ጊዜዋን እስክታሳልፍ ድረስ ቍጣን ታገሣት፤ ኋላም ደስ ታሰኝሃለች። 23 ጊዜውን እስክታገኝ ድረስ ነገርህን ሰውር፤ ብዙ ሰዎችም ጥበብህን ይናገራሉ። 24 በጥበብ መዛግብት የምሳሌ ትምህርት አለ። ኀጢአተኛ እግዚአብሔርን የሚፈራውን ይጸየፈዋል። 25 ጥበብን ከወደድሃት ትእዛዞቹን ጠብቅ፤ እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥሃል። 26 ጥበብም፥ ዕውቀትም፥ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ፈቃዱም ሃይማኖትና የዋሀት ነው። 27 እግዚአብሔርን መፍራትን አትዘንጋ። 28 እየተጠራጠርህ እግዚአብሔርን በሁለት ልብ አታገልግለው። 29 በሰው አፍ አትውደቅ፥ ከንፈሮችህንም ጠብቅ። 30 እንዳቷረድ ሰውነትህም እንዳትወድቅ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ እግዚአብሔርም የሰወርኸውን ይገልጥብሃል። እግዚአብሔርን በመፍራት አልመጣህምና፥ በልብህም ሽንገላ ሞልትዋልና በብዙዎች ሰዎች መካከል ይጥልሃል። |