Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ተግሣጽ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ወዳጆች ያለ ጥርጥር የጻፉት የተለያየ የሰሎሞን ተግሣጽ ነው። 2 የእግዚአብሔር ክብር ነገርን ይሰውራል፥ የንጉሥ ክብር ግን ነገርን ያከብራል። 3 ሰማይ ከፍ ያለ ነው፥ ምድርም ጥልቅ ነው፥ የንጉሥ ልብም እንዲሁ አይታወቅም። 4 ያልጠራውን ብር አጥራው፥ ፈጽሞም ይጠራል። 5 ከንጉሡ ፊት ክፉዎችን አጥፋ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ይቀናል። 6 በንጉሥ ፊት አትታበይ፥ በእግዚአብሔርም ፊት አትመጻደቅ፥ በመኳንንት ስፍራ አትቁም፤ 7 በመኰንን ፊት ከምቷረድ፦ ወደዚህ ከፍ በል ብትባል ይሻልሃልና፥ ዐይኖችህ ያዩትን ተናገር። 8 ኋላ እንዳትጸጸት፥ ለጥል ፈጥነህ አትውጣ። ክርክርን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፥ ምሥጢሩንም አትግለጥ። 9 ባልንጀራህ በነቀፈህ ጊዜ ወደኋላህ ተመለስ፥ ባልንጀራህም እንዳይነቅፍህ ቸል አትበለው፥ ጠብህም ክርክርህም ከእርሱ አያርቅህም። 10 ምሥጢሩን ብትገልጥ ግን የሞት ያህል ይሆንብሃል፥ ጸጋና ወንድማማችነትም ነጻ ያደርጋል። ነገር ግን መዘባበቻ እንዳትሆን ራስህን ጠብቅ፤ በመልካም ሥራህም መንገዶችህን ጠብቅ። 11 በብር ጻሕል ላይ ያለ የወርቅ ዕንኰይ ያማረ እንደሚሆን፥ በየመልኩ የሚናገሩት ቃልም እንዲሁ ነው። 12 በወርቅ ጉትቻ ላይ ያለ ዋጋው ብዙ የሆነ ሰርድዮን የሚባል የዕንቍ ፈርጥ ያማረ እንደሆነ፥ እንደዚሁ የብልህ ነገር በሚሰማ ሰው ጆሮ ያማረ ነው። 13 በመከር ወራት በቈላ የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፥ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ይጠቅማል። የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና። 14 በሐሰተኛ ሀብት የሚመኩ ሁሉ፥ ዝናብ እንደሌላቸው ደመናትና ነፋሳት ናቸው። 15 የሕይወት ውበት በትዕግሥት ትነግሣለች፥ ልዝብ አንደበትም አጥንትን ትሰብራለች። 16 ልጄ ሆይ፥ አጥብቀህ እንዳትጠግብ፥ እንዳትተፋውም ማር ባገኘህ ጊዜ በልኩ ብላ። 17 እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም፥ እግርህን ወደ ባልጀራህ ቤት አታዘውትር። 18 በባልጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር፥ እንደ በትርና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ፍላጻ ነው። 19 የክፉ መንገድና የኀጢአተኛ እግር፥ በክፉ ቀን ይጠፋሉ። 20 መጻጻ ለቍስል እንደማይመች፥ እንደዚሁም በሥጋ ላይ የሚወርድ ነውር ልብን ያሳዝናል። ነቀዝ ዕንጨትን፥ ብልም ልብስን እንደሚበላው፥ እንደዚሁ ኀዘን የሰውን ልብ ትጐዳለች። 21 ጠላትህ ቢራብ አብላው፥ ቢጠማም አጠጣው። 22 ይህን ብታደርግ በራሱ ላይ ፍም ትሰበስባለህ፥ እግዚአብሔርም መልካም ዋጋህን ይመልስልሃል። 23 የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ፊትን የማያፍር ምላስም ያስቈጣል። 24 ከነዝናዛ ሴት ጋር ባማረ ቤት ከመቀመጥ፥ አንድ ጎኑ በፈረሰ ግንብ መቀመጥ ይሻላል። 25 የቀዘቀዘ ውኃ ለተጠማች ሰውነት መልካም እንደ ሆነ፥ ከሩቅ ሀገር የመጣ የምሥራችም እንዲሁ መልካም ነው። 26 በኃጥኣን ፊት የጻድቅ መውደቅ፥ ጕድጓድን እንደ መዝጋትና የውኃ መውጫን እንደ ማጥፋት ነው። 27 ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም የራስን ክብር መፈለግ አያስከብርም። 28 ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥ ያለ ምክር የሚኖር ሰው እንዲሁ ነው። |