መዝሙር 80 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት የአሳፍ መዝሙር። 1 በረዳታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ። 2 ዝማሬውን አንሡ ከበሮውንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፤ 3 በመባቻ ቀን በታወቀችው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ 4 ለእስራኤል ሥርዐቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ ነውና። 5 ወደ ግብፅ ሀገር በሄደ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክርን አቆመ። የማያውቀውን ቋንቋ ሰማ። 6 ጀርባውን ከመስገጃቸው መለሰ፥ እጆቹም በቅርጫት ተገዙ። 7 በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ፥ አዳንሁህም፥ በተሰወረ ዐውሎም መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ። 8 ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ እነግርሃለሁም፤ እስራኤል ሆይ፥ እመሰክርልሃለሁ። 9 አንተስ ብትሰማኝ የድንገት አምላክ አልሆንህም፥ ለሌላ አምላክም አትስገድ። 10 ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤ አፍህን አስፋ፥ እሞላዋለሁም። 11 ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላደመጡኝም። 12 እንደ ሥራቸው ላክሁባቸው፥ በልባቸውም ዐሳብ ሄዱ። 13 ሕዝቤስ ቃሌን ሰምተውኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፤ 14 ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፤ 15 የእግዚአብሔር ጠላቶችስ ዋሽተውት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘለዓለም ይሆናል፤ 16 ከስንዴም ስብ አበላቸው፥ ከዓለቱም ማር አጠገባቸው። |