መዝሙር 78 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአሳፍ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ፤ ቤተ መቅደስህንም አረከሱ፥ ኢየሩሳሌምንም እንደ ተክል ጠባቂ ጎጆ አደረጉአት። 2 የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ፥ የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት፤ 3 ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፥ የሚቀብራቸውም አጡ። 4 ለጎረቤቶቻችንም ስድብ ሆንን፥ በዙሪያችንም ላሉ ሣቅና መዘበቻ። 5 አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘለዓለም ትቈጣለህ? ቅንዐትህም እንደ እሳት ይነድዳል? 6 በማያውቁህም አሕዛብ ላይ ስምህንም በማትጠራ መንግሥት ላይ መዓትህን አፍስስ፤ 7 ያዕቆብን በልተውታልና፥ ስፍራውንም ባድማ አድርገዋልና። 8 የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ በቶሎ ያግኘን፥ እጅግ ተቸግረናልና። 9 አምላካችንና መድኀኒታችን ሆይ፥ ርዳን፥ ስለ ስምህ ክብር አቤቱ፥ ታደገን፥ ስለ ስምህም ኀጢአታችንን አስተስርይልን። 10 አሕዛብ፥ “አምላካቸው ወዴት ነው?” እንዳይሉን፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዐይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይዩ። 11 የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት የተገደሉትን ሰዎች ልጆች ጠብቃቸው። 12 አቤቱ፥ የተገዳደሩህን መገዳደራቸውን፥ ለጎረቤቶቻችን ሰባት እጥፍ በብብታቸው ክፈላቸው። 13 እኛ ሕዝብህ ግን፥ የማሰማሪያህም በጎች፥ ለዘለዓለም እናመሰግንሃለን፤ ለልጅ ልጅም ምስጋናህን እንናገራለን። |