መዝሙር 75 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ስለ አሦራውያን የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ሆነ። 2 በሀገሩም በሰላም ኖረ፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው፤ 3 በዚያም የቀስትን ኀይል፥ ጋሻን፥ ጦርንና ሰልፍንም ሰበረ፤ በዚያም ቀንዶችን ሰበረ። 4 አንተ በዘለዓለም ተራሮች ሆነህ በድንቅ ታበራለህ። 5 ልበ ሰነፎች ሁሉ ደነገጡ፥ ሕልምን አለሙ፥ ያገኙት ግን የለም፤ ሰው ሁሉ ለእጁ ባለጠግነት ነው። 6 የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ ከተግሣጽህ የተነሣ ፈረሰኞች ሁሉ አንቀላፉ። 7 አንተ ግን፥ ግሩም ነህ፤ ቍጣህን ማን ይቃወማል? 8 ፍርድን ከሰማይ ታሰማለህ። ምድር ፈራች፥ ዝምም አለች፥ 9 ልበ የዋሃንን ሁሉ ያድን ዘንድ፥ እግዚአብሔር ለፍርድ በተነሣ ጊዜ። 10 ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ። 11 ለአምላካችን ለአግዚአብሔር ስእለትን ሰጡ፤ በዙሪያውም ያሉ ሁሉ እጅ መንሻን ለሚያስፈራው ያገባሉ። 12 የአለቆችን ነፍስ ያወጣል፤ በምድርም ነገሥታት ዘንድ ያስፈራል። |