መዝሙር 70 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አስቀድመው ስለ ተማረኩ ስለ አሚናዳብ ልጆች የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘለዓለም አላፍርም። 2 በጽድቅህ አስጥለኝ፥ ታደገኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ። 3 በጠንካራ ቦታ ታድነኝ ዘንድ አምላኬና መድኀኒቴ ሁነኝ፤ ኀይሌና መጠጊያዬ አንተ ነህና። 4 አምላኬ ከኃጥኣን እጅ፥ ከዐመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ። 5 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ ጌታዬ ሆይ፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ ተስፋ አደረግሁህ። 6 በእናቴ ማኅፀን በአንተ ጸናሁ፥ በማኅፀን ውስጥም አንተ ሸሸግኸኝ፤ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ። 7 ለብዙዎች እንደ ጥንግ ሆንሁ፤ አንተ ግን ረዳቴና ኀይሌ ነህ። 8 አፌን በምስጋና ምላ ሁልጊዜ ምስጋናህንና የክብርህን ገናናነት አመሰግን ዘንድ። 9 በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አምላኬ አትተወኝ። 10 ጠላቶቼ በእኔ ላይ ተናግረዋልና፥ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ፦ 11 “እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት።” 12 አምላኬ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ተመልከት። 13 ነፍሴን የሚያጣሏት ይፈሩ፥ ይዋረዱም፥ ጉዳቴንም የሚፈልጉ ዕፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ። 14 እኔ ግን አቤቱ ሁልጊዜ ተስፋ አደርግሃለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ። 15 አፌ ጽድቅህን፥ ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል። ሥራን አላውቅምና 16 በእግዚአብሔር ኀይል እገባለሁ፤ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ። 17 አምላኬ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ክብርህን እናገራለሁ። 18 አምላኬ ሆይ እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኀይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አትተወኝ። 19 አቤቱ፥ እስከ አርያም ታላላቅ ነገሮችን አደረግህ፤ አምላክ ሆይ፥ እንዳንተ ያለ ማን ነው? 20 ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመልሰህም ሕያው አደረግኸኝ፤ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኸኝ። 21 ጽድቅህንም አበዛኸው። ደስ ታሰኘኝም ዘንድ ተመለስህ። ከምድር ጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ። 22 እኔም በመዝሙር መሣሪያ ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። 23 ዝማሬን ባቀረብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼን ደስ ይላቸዋል፥ ነፍሴንም አንተ አዳንሃት። 24 ክፉን ለእኔ የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ፥ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል። |