መዝሙር 61 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ ስለ ኤዶታም የዳዊት መዝሙር። 1 ነፍሴ ለእግዚአብሔር የምትገዛ አይደለችምን? መድኀኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና። 2 እርሱ አምላኬ መድኀኒቴም ነውና፤ እርሱ ረዳቴ ነው ሁልጊዜም አልታወክም። 3 እስከ መቼ በሰው ላይ ትቆማላችሁ? እናንተ ሁላችሁ እንዳዘነበለ ግድግዳ እንደ ፈረሰም ቅጥር ትገድሉታላችሁ። 4 ነገር ግን ክብሬን ይሽሩ ዘንድ መከሩ፥ በጥሜም ሮጥሁ፤ በአፋቸው ይባርካሉ፥ በልባቸውም ይረግማሉ። 5 ነገር ግን ነፍሴ፥ ለእግዚአብሔር ትገዛለች፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና። 6 እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ ረዳቴ ነውና፥ አልታወክም። 7 መድኃኒቴ በእግዚአብሔር ነው፤ ክብሬም በእግዚአብሔር ነው፥ የረድኤቴ አምላክ፥ ተስፋዬም እግዚአብሔር ነው። 8 የአሕዛብ ማኅበር ሁላችሁ፥ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፥ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው። 9 ነገር ግን የሰው ልጆች ሁሉ ከንቱ ናቸው፥ የሰው ልጆችም ሐሰተኞች ናቸው፤ በሚዛንም ይበድላሉ፥ እነርሱስ በፍጹም ከንቱ ናቸው። 10 ዐመፃን ተስፋ አታድርጉ፥ ቅሚያንም አትተማመኑት፤ ባለጠግነት ቢበዛ ልባችሁን አታኩሩ። 11 እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ይቅርታ የእግዚአብሔር ነውና፥ 12 አቤቱ፥ ኀይልም ያንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህና። |