መዝሙር 60 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች የዳዊት መዝሙር። 1 አምላኬ ሆይ፥ ልመናዬን ስማኝ፥ ጸሎቴንም አድምጠኝ። 2 ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በድንጋይ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ። 3 በጠላት ፊት ጽኑ ግንብ ነህ፤ ተስፋዬም ሆነኽልኛልና መራኸኝ። 4 በድንኳንህ ለዘለዓለም እኖራለሁ፤ በክንፎችህ ጥላም እጋረዳለሁ፤ 5 አምላኬ፥ አንተ ጸሎቴን ሰምተሃልና፤ ለሚፈሩህም ርስትን ሰጠሃቸው። 6 ለንጉሥ ከቀን በላይ ቀንን ትጨምራለህ፥ ዓመታቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሆናሉ። 7 በእግዚአብሔርም ፊት ለዘለዓለም ይኖራል፤ ይቅርታውንና ጽድቁን ማን ይፈልጋል? 8 እንዲሁ ለስምህ ለዘለዓለም እዘምራለሁ ምኞቴን ሁልጊዜ ትሰጠኝ ዘንድ። |