መዝሙር 59 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የሶርያን ሁለቱን ወንዞችና የሶርያን ሶባልን ባቃጠለ ጊዜ ኢዮአብም ተመልሶ ከኤዶማውያን ሰዎች በጨው ሸለቆ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎችን በገደለ ጊዜ ለትምህርት የዳዊት ቅኔ። 1 አቤቱ፥ ጣልኸን አፈረስኸንም፤ ገረፍኸን፥ ይቅርም አልኸን። 2 ምድርን አናወጥሃት፥ አወክሃትም፤ ተናውጣለችና ቍስልዋን ፈወስኻት። 3 ለሕዝብህ ጭንቅን አሳየሃቸው፥ አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን። 4 ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፥ ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ። 5 ወዳጆችህም፥ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ ስማኝም። 6 እግዚአብሔር በመቅደሱ ተናገረ፤ ደስ ይለኛል፥ ምርኮንም እካፈላለሁ፥ የሸለቆ ቦታዎችን እሰፍራለሁ። 7 ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው፤ 8 ካህን ሞአብም ተስፋዬ ነው በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤምም ይገዙልኛል። 9 ቅጥር ወደ አለባት ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል? 10 አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላካችን ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም። 11 በመከራችን ረድኤትን ስጠን፥ በሰውም መታመን ከንቱ ነው። 12 በእግዚአብሔር ኀይልን እናደርጋለን፤ እርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል። |