መዝሙር 58 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ አታጥፋ። ሳኦል ይገድሉት ዘንድ ቤቱን እንዲጠብቁ በላከ ጊዜ የዳዊት ቅኔ። 1 አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶች አድነኝ፤ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ። 2 ከዐመፅ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ። 3 እነሆ፥ ነፍሴን አድድነዋታልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተነሡ፤ አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኀጢአቴም አይደለም። 4 ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም። 5 አንተም አቤቱ፥ የኀያላን አምላክ፥ የእስራኤል ንጉሥ፥ አሕዛብን ሁሉ ጐብኛቸው፥ ይቅርም በላቸው፤ ዐመፅ የሚያደርጉትን ሁሉ ግን አትማራቸው። 6 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። 7 እነሆ፥ በአፋቸው ይናገራሉ፤ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፤ 8 የምትሰማቸው አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛቡንም ሁሉ ትንቃቸዋለህ፥ 9 ኀይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ፥ አንተ አምላኬና መጠጊያዬ ነህና። 10 የአምላኬ ይቅርታው ይድረሰኝ አምላኬ በጠላቶቼ ላይ አሳየኝ። 11 ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ አቤቱ፥ አምላኬና ረዳቴ፥ በኀይልህ በትናቸው፥ አዋርዳቸውም። 12 ስለ አፋቸው ኀጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ ከመርገማቸውና ከሐሰታቸው የተነሣ፥ ፍጻሜያቸው ይታወቃል። 13 ኋላ በሚመጣ መቅሠፍት ያልቃሉ፤ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲገዛ ይወቁ። 14 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። 15 እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፤ የጠገቡ እንደ ሆነም ያንጐራጕራሉ። 16 እኔ ግን ለኀይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም በማለዳ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኽልኛልና። 17 አንተ ረዳቴ ነህ፥ ለአንተም ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ ነህና አምላኪዬ ምሕረቴም ነህና። |