መዝሙር 56 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ አታጥፋ። ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ የዳዊት ቅኔ። 1 ይቅር በለኝ፥ አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፤ ኀጢአት እስክታልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ። 2 ወደ ልዑል እግዚአብሔር፥ ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር እጮኻለሁ። 3 ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና ጽድቁን ላከ። 4 ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬም ተኛሁ፤ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ ነው፥ አንደበታቸውም የተሳለ ሾተል ነው። 5 እግዚአብሔር በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ክብሩም በምድር ሁሉ ላይ ነው። 6 ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ሰውነቴንም አጐበጡአት፤ ጕድጓድን በፊቴ ቈፈሩ፥ በውስጡም ወደቁ። 7 ልቤ ጽኑዕ ነው፥ አቤቱ ልቤ ጽኑዕ ነው፥ አመሰግናለሁ፥ እዘምራለሁም። 8 ክብሬ ይነሣ፥ በበገናና በመሰንቆ ይነሣ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ። 9 አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፤ 10 ምሕረትህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ ጽድቅህም እስከ ደመናት ድረስ። 11 እግዚአብሔር በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ክብሩም በምድር ሁሉ ላይ ነው። |