መዝሙር 55 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ ከቅዱሳን ስለ ራቁ ሕዝብ ፍልስጥኤማውያን በጌት በያዙት ጊዜ የዳዊት ቅኔ። 1 አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ይቅር በለኝ፤ ሁልጊዜም ሰልፍ አስጨንቆኛል። 2 ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ጠላቶች ረገጡኝ፥ የሚዋጉኝ በዝተዋልና ፈራሁ። 3 እኔ ግን አቤቱ በአንተ ታመንሁ። 4 በእግዚአብሔር ቃሉን አከብራለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? 5 ሁልጊዜ ቃሎችን ይጸየፉብኛል፤ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው። 6 ይሸምቁብኛል፥ ይሸሸጉኝማል፥ እነርሱም ተረከዜን ይመለካከታሉ፥ ሁልጊዜም ነፍሴን ይሸምቁባታል። 7 በምንም ምን አታድናቸውም፤ አሕዛብን በመዓትህ ትጥላቸዋለህ። 8 አምላኬ ሆይ፥ ሕይወቴን እነግርሃለሁ፤ እንባዬንም እንደ ትእዛዝህ በፊትህ አኖርሁ። 9 በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶች ወደ ኋላቸው ይመለሱ፤ አንተ አምላኬ እንደ ሆንህ እነሆ፥ ዐወቅሁ። 10 በእግዚአብሔር ቃሌን አከብራለሁ፤ የተናገርሁትም በእግዚአብሔር ዘንድ ይከብራል። 11 በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል? 12 አቤቱ፥ የምስጋና ስእለት የምሰጥህ ከእኔ ዘንድ ነው፤ 13 ነፍሴን ከሞት፥ ዐይኖቼን ከዕንባ፥ እግሮቼንም ከድጥ አድነሃልና፥ በሕያዋን ሀገር እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ። |