መዝሙር 54 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች የዳዊት ትምህርት። 1 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጠኝ፥ ልመናዬንም ቸል አትበለኝ። 2 ተመልከተኝ፥ ስማኝም፤ አዘንሁ፥ ደነገጥሁ፥ ተናወጥሁም፤ 3 ከጠላት ድምፅ፥ ከኀጢአተኛም ማሠቃየት የተነሣ፥ ዐመፃን በላዬ መልሰውብኛልና፥ ሊያጠፉኝም ተነሥተውብኛልና። 4 ልቤ በላዬ ደነገጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም መጣብኝ። 5 ፍርሃትና እንቅጥቅጥ ያዙኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ። 6 በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ አልሁ፥ 7 እነሆ፥ ኮብልዬ በራቅሁ፥ በምድረ በዳም በኖርሁ፤ 8 እንደ ዐውሎ ነፋስ ከሆነው ከነፍሴ መቅበዝበዝ የሚያድነኝን ተስፋ አደርገዋለሁ። 9 አቤቱ፥ ዐመፃንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይችአለሁና አስጥማቸው፥ አንደበታቸውንም ቍረጥ። 10 በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዐመፃና ድካም ኀጢአትም በመካከልዋ ነው፤ 11 ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቅም። 12 ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፤ የሚጠላኝም አፉን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር። 13 አንተ ሰው፥ አንተ ግን እንደ ራሴ ነበርህ፥ ባልንጀራዬና የማውቅህ ወዳጄም ነበርህ፤ 14 መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ ነበርህ፤ በአንድ ልብ ወደ እግዚአብሔር ቤት ተራመድን። 15 ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉም ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና። 16 እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እግዚአብሔርም ሰማኝ። 17 በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ አስረዳለሁ፥ ቃሌንም አይሰሙኝም። 18 ከእኔ ጋር ካሉት ይበዛሉና ከሚቃረቡኝ ነፍሴን በሰላም አድናት። 19 ቤዛ የላቸውምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ዓለም ሳይፈጠር የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቍላቸዋል። 20 ፍዳን ለማምጣት እጁን ዘረጋ፤ ኪዳኑንም አረከሱ። 21 ከፊቱም ቍጣ የተነሣ ተለያዩ፥ ልቡም ቀረበ፤ ቃሉም ከቅቤ ይልቅ ለሰለሰ፤ እነርሱ ግን እንደሚያሰጥም ማዕበል ናቸው። 22 ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይመግብሃል፤ ለጻድቁም ለዘለዓለም ሁከትን አይሰጠውም። 23 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ አውርዳቸው፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸውን አያጋምሱም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ እታመንሃለሁ። |