መዝሙር 53 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል፦ እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኀይልህም ፍረድልኝ። 2 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤ 3 ባዕዳን በእኔ ላይ ቆመዋልና፥ ኀያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርንም በፊታቸው አላደረጉትም። 4 እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ነፍሴን ያድናታል። 5 ክፋትን ወደ ጠላቶች ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው። 6 ከፈቃዴ የተነሣ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና፥ ስምህን አመሰግናለሁ፤ 7 ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዐይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና። |