መዝሙር 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በኀይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህም እጅግ ሐሤትን ያደርጋል። 2 የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው፥ የከንፈሮቹንም ልመና አልከለከልኸውም። 3 በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፤ ከክቡር ዕንቍ የሆነ ዘውድንም በራሱ ላይ አኖርህ። 4 ሕይወትን ለመነህ፥ ሰጠኸውም፥ ለረዥም ዘመን ለዘለዓለሙ። 5 በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፤ ክብርንና ምስጋናን ጨመርህለት። 6 የዘለዓለም በረከትን ሰጥተኸዋልና፥ በፊትህም ደስታ ደስ ታሰኘዋለህ። 7 ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም። 8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው። 9 ፊትህ በተቈጣ ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ አቤቱ፥ በቍጣህ አውካቸው፥ እሳትም ትብላቸው። 10 ፍሬያቸውን ከምድር፥ ዘራቸውንም ከሰው ልጆች አጥፋ። 11 ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ መወሰን የማይቻላቸውንም ምክር ዐሰቡ። 12 ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፊታቸውን ለመዓትህ ጊዜ ታዘጋጃለህ። 13 አቤቱ፥ በኀይልህ ከፍ ከፍ አልህ፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን፤ እንዘምርማለን። |