መዝሙር 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ እግዚአብሔር ባዳነው ቀን በዚህ መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር የተናገረው የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በኀይሌ እወድድሃለሁ። 2 እግዚአብሔር ኀይሌ፥ አምባዬ፥ መድኀኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬም ነው። 3 እግዚአብሔርን በጠራሁት ጊዜ ከጠላቶቼ እድናለሁ። 4 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዐመፅ ፈሳሽም አወከኝ፤ 5 የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ። 6 በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ በቤተ መቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። 7 ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔር ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። 8 ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ። 9 ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፥ ጭጋግ ከእግሩ በታች ነበረ። 10 በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ። 11 መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ ውኃዎች በደመናዎች ውስጥ ጠቈሩ። 12 በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም በፊቱ አለፉ። 13 እግዚአብሔርም በሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። 14 ፍላጻውን ላከ፥ በተናቸውም፤ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም። 15 አቤቱ፥ ከተግሣጽህ፥ ከመዓትህም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። 16 ከአርያም ላከ፥ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። 17 ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። 18 በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን መጠጊያዬ ሆነ። 19 ወደ ሰፊ ሥፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ። 20 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይሰጠኛል፤ እንደ እጆቼ ንጽሕናም ይከፍለኛል። 21 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ አምላኬንም አልበደልሁም። 22 ፍርዱ ሁሉ ሁልጊዜ በፊቴ ነበረና፥ ጽድቁም ከእኔ አልራቀም። 23 ከእርሱ ጋር ንጹሕ እሆናለሁ። ከኀጢአቴም እጠበቃለሁ። 24 እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ ይሰጠኛል። እንደ እጆቼም ንጽሕና በዐይኖቹ ፊት ይከፍለኛል። 25 ከጻድቅ ሰው ጋር ጻድቅ ትሆናለህ፤ ከቅን ሰው ጋርም ቅን ትሆናለህ፤ 26 ከንጹሕም ሰው ጋር ንጹሕ ትሆናለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ትሆናለህ፥ 27 አንተ የተዋረደውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዐይኖች ግን ታዋርዳለህ። 28 አቤቱ አንተ መብራቴን ታበራለህና፤ አምላኬ ጨለማዬን ያበራል። 29 በአንተ ከጥፋት እድናለሁና፥ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ። 30 የአምላኬ መንገዱ ንጹሕ ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ መታመኛቸው ነው። 31 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር እግዚአብሔር ማን ነው? 32 ኀይልን የሚያስታጥቀኝ እግዚአብሔር ነው፥ መንገዴንም ንጹሕ የሚያደርጋት፥ 33 እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች የሚያረታ በከፍታም ቦታ የሚያቆመኝ፥ 34 እጆቼን ሰልፍ የሚያስተምር፤ ለክንዴም የናስ ቀስት አደረገ። 35 ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኝ። ቀኝህም ተቀበለኝ፥ ትምህርትህም ለዘለዓለም ያጠናኛል። የሚያስተምረኝም ተግሣጽህ ነው። 36 አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ ሰኰናዬም አልደከመም። 37 ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። 38 አስጨንቃቸዋለሁ፤ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። 39 በሰልፍም ኀይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ትጥላቸዋለህ። 40 የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። 41 ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አጡ። ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፥ አልሰማቸውም። 42 በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ። 43 ከሕዝብ ክርክር አድነኝ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። 44 በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፤ የባዕድ ልጆች ዋሹኝ። 45 የባዕድ ልጆች አረጁ፥ በመገንዳቸውም ተሰናከሉ። 46 እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም ቡሩክ ነው፥ የመድኀኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ አለ። 47 አምላኬ በቀሌን ይመልስልኛል። አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል። 48 ከጥፉዎች ጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፤ በእኔ ላይ ከቆሙትም ከፍ ከፍ የሚያደርገኝ እርሱ ነው፥ ከግፈኛ ሰው አድነኝ። 49 አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ። 50 የንጉሡን መድኀኒት ታላቅ ያደርጋታል፥ ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊት፥ ለዘሩም እስከ ዘለዓለም ያደርጋል። |