መዝሙር 151 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከቍጥር የወጣ መዝሙር ስለ ራሱ። 1 ከወንድሞቼ ይልቅ እኔ ትንሽ ነበርሁ፥ በአባቴም ቤት ወጣት ነበርሁ፥ ያባቴንም በጎች እጠብቅ ነበር። 2 እጆቼ መሰንቆ ይመቱ ነበር። ጣቶቼም በገና ይደረድሩ ነበር። 3 ለጌታዬ ማን ነገረው? እርሱ እግዚአብሔር እርሱ ሰማኝ። 4 እርሱ መልአኩን ልኮ አዳነኝ፥ የአባቴን በጎች ከምጠብቅበት ወሰደኝ፤ የተቀደሰ ቅባትን ቀባኝ፤ 5 ወንድሞቼ ግን፥ ያማሩና ያደጉ ነበሩ። እግዚአብሔር ግን በእነርሱ ደስ አላለውም። 6 ልዩ ወገንን ልገጥመው ወጣሁ። በረከሱ ጣዖቶቹም ረገመኝ። 7 እኔም ከወንዝ ሦስት ድንጋዮችን አነሣሁ፥ ግንባሩንም በወንጭፍ መታሁት። ያንጊዜም በእግዚአብሔር ኀይል ወደቀ። 8 በላዩ የነበረውንም ሰይፍ ወሰድሁ፥ የጎልያድንም ቸብቸቦ ቈረጥሁ። ከእስራኤል ልጆችም ስድብን አራቅሁ። |