መዝሙር 148 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር። ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም ያመሰግኑታል፤ 2 መላእክቱ ሁሉ ያመሰግኑታል፤ ሠራዊቱ ሁሉ ያመሰግኑታል። 3 ፀሐይና ጨረቃ ያመሰግኑታል፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ ያመሰግኑታል። 4 ሰማየ ሰማያት፥ ከሰማያት በላይ ያለ ውኃም ያመሰግኑታል። 5 የእግዚአብሔርንም ስም ያመሰግናሉ። እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑ፤ እርሱ አዝዞአልና፥ ተፈጠሩ፤ 6 ለዘለዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጣቸው፥ አላለፉምም። 7 እባቦችና ጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት፤ 8 እሳትና በረዶ፥ አመዳይና ውርጭ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም፤ 9 ተራሮችና ኮረብቶችም ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ፤ 10 አራዊትም፥ እንስሳትም ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾችም፥ የሚበርሩ ወፎችም፤ 11 የምድር ነገሥታት፥ አሕዛብም ሁሉ፥ አለቆች፥ የምድርም ፈራጆች ሁሉ፤ 12 ጐልማሶችና ደናግል፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ 13 የእግዚአብሔርን ስም ያመሰግናሉ። ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ በሰማይና በምድር ያመሰግኑታል። 14 የሕዝቡንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ የጻድቃኑንም ሁሉ ምስጋና ወደ እርሱ ለቀረበ ለእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል። |