መዝሙር 142 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ልጁ ባሳደደው ጊዜ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ በእውነትህ ልመናዬን አድምጥ፥ በጽድቅህም መልስልኝ። 2 ሕያው ሁሉ በፊትህ አይጸድቅምና ከባሪያህ ጋር ወደ ክርክር አትግባ። 3 ጠላት ነፍሴን ከብቦአታልና ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አዋርዶአታል፥ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኖሩኝ። 4 ሰውነቴ በላዬ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ። 5 የቀድሞውን ዘመን ዐሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አነበብሁ፤ የእጅህንም ሥራ አነብባለሁ። 6 እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። 7 አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፥ ሰውነቴ አልቃለች፤ ፊትህንም ከእኔ አትመልስ፥ ወደ ጕድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን። 8 አቤቱ፥ አንተን ታምኛለሁና፥ በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድባትን መንገድ ምራኝ። 9 አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማጽኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ። 10 አቤቱ፥ አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ። 11 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ ስለ ጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት። 12 በፈቃድህ ጠላቶቼን አጥፋቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው። |