መዝሙር 131 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የመዓርግ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ዳዊትን፥ ገርነቱንም ሁሉ ዐስብ፤ 2 ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦ 3 “ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ መኝታዬም አልጋ አልወጣም፥ 4 ለዐይኖቼም መኝታን፥ ለቅንድቦቼም እንቅልፍን፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ 5 የእግዚአብሔርን ቦታ፥ የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስካገኝ ድረስ” ብሎ እንደ ተሳለ ዐስብ። 6 እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው። 7 እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን፤ የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን። 8 አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት። 9 ካህናትህ ጽድቅን ይለብሳሉ፥ ጻድቃንህም ደስ ይላቸዋል። 10 ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት ቀብተህ ካነገሥኸው ፊትህን አትመልስ። 11 እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲህ ሲል በእውነት ማለ፥ አይጸጸትምም፥ “ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁና 12 ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ።” 13 እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ 14 “ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። 15 ባልቴቶችዋን እጅግ እባርካቸዋለሁ፥ ድሆችዋንም እህልን አጠግባቸዋለሁ፥ 16 ካህናቷንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ጻድቃኖችዋም እጅግ ደስ ይላቸዋል። 17 በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ቀብቼ ላነገሥሁትም መብራትን አዘጋጃለሁ። 18 ጠላቶቹንም እፍረትን አለብሳቸዋለሁ፤ በእርሱም ቅድስናዬ ያፈራል።” |