መዝሙር 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 ሰነፍ በልቡ፥ “እግዚአብሔር የለም” ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐሰቈሉም፤ በጎ ነገርን የሚሠራት የለም። አንድም እንኳ የለም። 2 የሚያስተውል፥ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። 3 ሁሉ ተስተካክሎ በአንድነት ዐመፀ፤ በጎ ነገርን የሚሠራት የለም፤ አንድም እንኳ የለም። 4 ጕሮሮኣቸው እንደ መቃብር የተከፈተ ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ 5 ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መራራ ነው፥ መርገምንም ተሞልቶአል፤ 6 ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዐይናቸው ፊት የለም። 7 ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ፥ ኀጢአትን የሚሠሩ ሁሉ አያውቁም። እግዚአብሔርንም አይጠሩትም። 8 በዚያም ፈሩ፥ የማያስፈራውም አስፈራቸው። እግዚአብሔር በጻድቃን ትውልድ ዘንድ ነውና። 9 የድሆችን ምክር አሳፈራችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ተስፋቸው ነው። 10 ከጽዮን መድኀኒትን ለእስራኤል ማን ይሰጣል? እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል፥ እስራኤልም ሐሤትን ያደርጋል። |