መዝሙር 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትመልሳለህ? 2 እስከ መቼ በነፍሴ ኀዘንን አኖራለሁ? እስከ መቼ ልቤ ሁልጊዜ ትጨነቅብኛለች? እስከ መቼ ጠላቶች በላዬ ይታበያሉ? 3 አቤቱ አምላኬ፥ ተመልከተኝ ስማኝም፤ ለሞትም እንዳያንቀላፉ ዐይኖቼን አብራቸው። ጠላቶቼም አሸነፍነው እንዳይሉ፥ 4 የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ 5 እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ፥ ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል። 6 የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ። |