መዝሙር 114 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። 2 ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ። 3 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትና መከራ አገኘኝ። 4 የእግዚአብሔርንም ስም ጠራሁ፦ አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። 5 እግዚአብሔር መሓሪና ጻድቅ ነው። አምላካችን ይቅር ባይ ነው። 6 እግዚአብሔር ሕፃናትን ይጠብቃል፤ ተቸገርሁ እርሱም አዳነኝ። 7 ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር ረዳትሽ ነውና፤ 8 ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከድጥ አድኖአልና። 9 በሕያዋን ሀገር እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ። |