መዝሙር 112 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሃሌ ሉያ። 1 የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ። 2 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ የእግዚአብሔር ስሙ ቡሩክ ይሁን። 3 ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስሙ ይመስገን። 4 እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ልዑል ነው፥ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው። 5 እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በልዕልና የሚኖር። 6 በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ 7 ድሃውን ከምድር የሚያነሣ፥ ምስኪኑንም ከመሬት ከፍ ከፍ የሚያደርግ፤ 8 ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ 9 መካኒቱን በቤቱ የሚያኖራት፥ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። |