ምሳሌ 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ብዙ ደስታ ከሞላበትና ከክርክር ጋር የዐመፃ ፍሪዳ ካለበት ቤት ይልቅ፥ ከሰላም ጋር ደረቅ ቍራሽ ይሻላል። 2 ብልህ አገልጋይ አላዋቂዎች ጌቶችን ይገዛል፥ ከወንድማማች ጋርም ርስትን ይካፈላል። 3 ብርና ወርቅ በከውር እንዲፈተን፥ የተመረጡ ሰዎች ልብም በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ ነው። 4 ክፉ ሰው ከሕግ ውጭ የሆኑትን ሰዎች አንደበት ይሰማል፤ ጻድቅ ግን የሐሰት ከንፈሮችን አይመለከትም። ለሚያምን በዓለም ያለው ገንዘቡ ነው፥ ለማያምን ግን መሐለቅ የለውም፥ 5 በድሃ የሚያላግጥ ፈጣሪውን ያነሣሣዋል፥ በሚጠፋም ላይ ደስ የሚለው ከፍርድ አይነጻም፥ የሚራራ ግን ምሕረትን ያገኛል። 6 የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው፤ የልጆችም ክብር አባቶቻቸው ናቸው። 7 የታመነች ከንፈር ለሰነፍ፥ የሐሰት ከንፈርም ለጻድቅ አትስማማውም። 8 ትምህርት ገንዘብ ለሚያደርጓት የባለሟልነት ዋጋ ናት፥ ወደ ተመለሰችበትም መንገድን ታቀናለታለች። 9 በደሉን የሚሰውር ሰው ዕርቅን ይሻል፤ በደሉን መሰወር የሚጠላ ግን ቤተሰቦችንና ወዳጆችን ይለያያል። 10 ትምክሕት የአስተዋይ ሰው ልቡናን ያሳዝነዋል፥ አላዋቂ ግን ተገርፎ ግርፋቱ አይታወቀውም፥ 11 ክፉ ሰው ሁሉ ጠብን ያነሣሣል፤ እግዚአብሔርም ምሕረት የሌለውን መልአክ ይልክበታል። 12 ዐዋቂ ሰው በትካዜ ውስጥ ይወድቃል፥ አላዋቂዎች ግን ክፉን ያስባሉ። 13 በመልካም ፋንታ ክፉን የሚመልስ፥ ክፉ ነገር ከቤቱ አይርቅም። 14 የጠብ መጀመሪያ ውኃን መድፈን ነው። የጽድቅ መጀመሪያ በነገር መሠልጠንን ይሰጣል፥ የችጋር አበጋዝ ጠብና ክርክር ነው። 15 ኃጥኡን ጻድቅ፥ ጻድቁንም ኃጥእ ብሎ መፍረድ በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰና የተናቀ ነው። 16 ለአላዋቂ ሰው ገንዘብ ለምንድን ነው? አላዋቂ ሰው ጥበብን ገንዘብ ማድረግ አይችልምና፥ ቤቱን የሚያስረዝም ሰው ለራሱ ጥፋትን ይሻል፤ ለመማርም የሚጨንቀው ወደ ክፉ ይወድቃል። 17 ሁልጊዜ ወዳጅ ይኑርህ፥ ወንድሞች በመከራ ጊዜ ጠቃሚዎች ይሆናሉ፥ ስለዚህ ይወለዳሉና። 18 አላዋቂ ሰው አጋና ይመታል፥ ለባልንጀራውም ዋስ እንደሚሆን በራሱ ደስ ይለዋል። 19 ክርክርን የሚወድድ በጠብ ደስ ይለዋል። 20 ጠማማ ልብ ያለው መልካም ነገርን አያገኝም፥ አንደበቱን የሚለዋውጥም በክፉ ላይ ይወድቃል። 21 የሰነፍ ልብ ገንዘብ ላደረጋት ኀዘን ናት፥ አባት ባልተማረ ልጁ ደስ አይለውም፥ ብልህ ልጅ ግን እናቱን ደስ ያሰኛል። 22 ደስ ያላት ልብ ፈውስን ታገኛለች፤ ኀዘንተኛ ሰው ግን አጥንቱን ያደርቃል። 23 መማለጃን በዐመፃ በብብቱ የሚቀበል መንገዶቹን አያቀናም፥ ክፉ ሰውም ከጽድቅ መንገዶች ይርቃል። 24 የብልህ ሰው ፊት ዐዋቂ ነው፤ የአላዋቂ ሰው ዐይኖች ግን በምድር ዳርቻ ናቸው። 25 አላዋቂ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፥ ለወለደችውም ኀዘን ነው። 26 ጻድቅን ሰው ማዋረድ መልካም አይደለም። በእውነት ለሚፈርዱም መዋሸት መልካም አይደለም። 27 ሻካራ ቃልን ከመናገር የሚከለክል ዐዋቂ ነው፥ ትዕግሥተኛ ሰውም ብልህ ነው። 28 አላዋቂ ጥበብን ቢጠይቅ ጥበብ ይሆነዋል፤ ዝም የሚል ሰውም ጥበበኛን ይመስላል። |