ምሳሌ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ ተግሣጽን የሚጠላ ግን ሰነፍ ነው። 2 የተሻለ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል። ዐመፀኛ ሰው ግን ቸል ይባላል። 3 ከዐመፃ የማይርቅ ሰው ይጠፋል፤ የጻድቃን ሥር ግን አይነቀልም። 4 ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ ክፉ ሴት ግን ነቀዝ እንጨትን እንደሚበላ እንዲዚሁ ባሏን ትጐዳለች። 5 የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፤ ኃጥኣን ግን ሽንገላን ያስተምራሉ። 6 የኃጥኣን ምክር ተንኮል ነው። የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል። 7 ኀጢአተኛ በተገለበጠበት ይጠፋል፥ የጻድቃን ቤቶች ግን ጸንተው ይኖራሉ። 8 የብልህ ሰው አንደበት በሰው ሁሉ ዘንድ ይመሰገናል፤ ልበ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል። 9 ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል። 10 ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኃጥኣን ምሕረት ግን አለመመጽወት ነው። 11 ምድሩን የሚያርሳት ሰው እንጀራን ይጠግባል፤ ቦዘኔነትን የሚከተል ግን የአእምሮ ድህነትን ይሰበስባል። በወይን ግብዣ ራሱን ደስ የሚያሰኝ ሰው በሰውነቱ ውርደትን ያመጣል። 12 የኃጥኣን ምኞት ክፋት ናት። የጻድቃን ሥር ግን የጸና ነው። 13 ኀጢአተኛ ሰው በከንፈሩ ኀጢአት ወደ ወጥመድ ይወድቃል፤ ጻድቅ ግን ከእርሱ ያመልጣል። አስፍቶ የሚመለከት ሰው ብዙ ምሕረትን ያገኛል። ድንገት በበር የሚገናኝ ግን ነፍሳትን ያስጨንቃል። 14 የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም የከንፈሩን ዋጋ ይቀበላል። 15 የሰነፎች መንገድ በፊታቸው የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። 16 ሰነፍ ቍጣውን በየቀኑ ይናገራል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። 17 ጻድቅ ሰው የተገለጠ እውነትን ያስተምራል፤ የክፉዎች ምስክርነት ግን ውሸት ነው። 18 በሐሰት የሚመሰክሩ በሰይፍ ይገድላሉ፤ በአፋቸው ሰይፍ አለና። የጠቢባን ምላስ ግን የቈሰለውን ይፈውሳል። 19 የጻድቃን ከንፈሮች ምስክርነትን ያቀናሉ፥ የሚቸኩል ምስክር ግን ክፉ አንደበት አለው። 20 ክፉን በሚያስብ ልብ ውስጥ ማታለል አለ፤ ሰላምን የሚወዱ ግን ደስ ይላቸዋል፥ 21 ጻድቅን ምንም ክፉ ነገር ደስ አያሰኘውም፤ ክፉዎች ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። 22 ሐሰተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። 23 ብልህ ሰው የጥበብ መንበር ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን መርገምን ያገኛል። 24 የተመረጡ ሰዎች እጅ ፈጥኖ ይገዛል፤ ሐሰተኞች ሰዎች ግን ለምርኮ ይሆናሉ። 25 የሚያስደነግጥ ቃል የጻድቅ ሰው ልቡናን ያውካል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል። 26 ራሱን የሚያውቅ ሰው ለራሱ ጻድቅ ነው፤ የክፉዎች ሥራ ግን መልካም አይደለም። የሚበድሉ ሰዎችን ክፉ ይከተላቸዋል፥ የኃጥኣን መንገዳቸውም ታስታቸዋለች። 27 ታካች ሰው አድኖ አይዝም። ንጹሕ ሰው ግን ክቡር ሀብት ነው። 28 በጽድቅ መንገድ ሕይወት አለ፥ ክፉን የሚያስቡ ሰዎች መንገዶች ግን ወደ ሞት ያወርዳሉ። |