ዘኍል 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንጹሓን ስላልሆኑ ሰዎች 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ በሰውነቱ የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ 3 እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከወንድ እስከ ሴት ከሰፈሩ አውጡአቸው።” 4 የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ። ስለ በደል ካሣ 5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወንድ ወይም ሴት ቸል ብለው ወይም ባለማወቅ ሰው ከሚሠራው ኀጢአት ሁሉ የሠሩት ቢኖር፥ 7 ያች ሰውነት ብትናዘዝ፥ ያደረገችውንም ኀጢአት ሁሉ ብትናገር የወሰደውን ዓይነቱን ሁሉ ይመልስ። አምስተኛ እጅም ለባለ ገንዘቡ ይጨምር። 8 ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዬው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፤ ይህም ስለ እርሱ ማስተስረያ ከሚደረግበት አውራ በግ ላይ ይጨመር። 9 የእስራኤልም ልጆች ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡአቸው የተቀደሱ ነገሮች ሁሉ የመጀመሪያው ለካህኑ ነው። 10 የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን።” ባልዋ ስለሚጠራጠራት ሴት 11 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥ 13 ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ ብታመነዝር፥ ከባልዋም ዐይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ 14 ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትያዝ፥ በባልዋም ላይ የቅንዐት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዐቱ መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፥ 15 ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፤ የኢፍ መስፈሪያም ዐሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዐት ቍርባን ነውና፥ ኀጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት። 16 “ካህኑም ያቀርባታል፤ በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤ 17 ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ማሰሮ ይወስዳል፤ ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤ 18 ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፤ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፤ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ የቅንዐት ቍርባን ያኖራል፤ በካህኑም እጅ ርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል። 19 ካህኑም ያምላታል፤ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል፦ ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ ርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤ 20 ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ወንድ ከአንቺ ጋር ተኝቶ እንደ ሆነ፤ 21 ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፤ ካህኑም ሴቲቱን እንዲህ ይበላት፦ እግዚአብሔር የተረገምሽ ያድርግሽ ጎንሽን ያረግፈው ዘንድ እግዚአብሔር ከሕዝብሽ መካከል ለይቶ ያጥፋሽ፤ ሆድሽን ይሰንጥቀው፤ 22 ርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ማኅፀንሽንም ይሰንጥቀው፤ ጎንሽም ይርገፍ። ሴቲቱም፦ ይሁን ይሁን ትላለች። 23 “ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጽፋቸዋል፤ በመርገሙም መራራ ውኃ ይደመስሳቸዋል፤ 24 የመርገሙን መራራ ውኃ ለሴቲቱ ያጠጣታል፤ የርግማኑም ውኃ ወደ ሆድዋ ይገባል። 25 ካህኑም የቅንዐቱን መሥዋዕት ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፤ ያንም መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ 26 ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ያን ውኃ ያጠጣታል። 27 ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ራስዋን አርክሳና ባልዋን ቸል ብላው ከሆነ፤ የመርገሙ መራራ ውኃ ወደ ሆድዋ ይገባል፤ ሆድዋንም ይሰነጥቀዋል፤ ጎኗም ይረግፋል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። 28 ራስዋን ያላረከሰች እንደ ሆነች፥ ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ያነጻታል፤ ልጆችንም ትወልዳለች። 29 “በባልዋ ላይ ለበደለችና ራስዋን ላረከሰች ሴት የቅንዐት ሕግ ይህ ነው፤ 30 በሰው ላይ የቅንዐት መንፈስ ቢመጣ፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፤ 31 ካህኑም ይህን ሕግ ሁሉ ያደርግባታል። ሰውየውም ከኀጢአት ንጹሕ ይሆናል፤ ሴቲቱም ኀጢአቷን ትሸከማለች።” |