ዘኍል 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የተስፋይቱ ምድር ወሰኖች 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ እነሆ እናንተ ወደ ከነዓን ምድር ትገባላችሁ፤ የከነዓንም ምድር ከአውራጃዎችዋ ጋር ለእናንተ ርስት ትሆናለች። 3 የአዜቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ በኤዶምያስ መያያዣ ይሆናል፤ የአዜብም ዳርቻ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤ 4 ዳርቻችሁም በአቅራቦን ዐቀበት በአዜብ በኩል ይዞራል፤ እስከ ኤናቅም ይደርሳል፤ መውጫውም በቃዴስ በርኔ በአዜብ በኩል ይሆናል፤ ወደ አራድ ሀገሮችም ይደርሳል፤ ወደ አሴሞናም ያልፋል፤ 5 ዳርቻውም ከአሴሞና ወደ ግብፅ ወንዝ ይዞራል፤ ወሰኑ ባሕሩ ይሆናል። 6 “ለባሕርም ዳርቻ ታላቁ ባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል፤ ይህ የባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል። 7 “በመስዕም በኩል ወሰናችሁ ከታላቁ ባሕር በተራራው በኩል ይሆንላችኋል። 8 ከተራራው እስከ ተራራው ድረስ ይሆንላችኋል፤ እስከ ኤማትም ይደርሳል፤ የዳርቻውም መውጫ በሰረደክ ይሆናል፤ 9 ዳርቻውም ወደ ዲፍሮና ያልፋል፤ መውጫውም አርሴናይን ይሆናል፤ በመስዕ በኩል ያለው ወሰናችሁም በዚህ ይሁናችሁ። 10 “በምሥራቅ በኩል ያለው ወሰናችሁም ከሴፋማ አርሴናይን ጀምሮ ነው። 11 ዳርቻውም ከሴፋማ በዐይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ አርቤላ ይወርዳል፤ እስከ ኬኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤ 12 ዳርቻውም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፤ መውጫውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ዳርቻዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።” 13 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ “እግዚአብሔር ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ይሰጡአቸው ዘንድ እንደ አዘዘ በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤ 14 የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል። 15 እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ወረሱ።” ምድሪቱን ለማከፋፈል ሐላፊነት የተሰጣቸው አለቆች 16 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ፤ ተናገረው፦ 17 “ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ። 18 ምድሪቱንም ርስት አድርገው የሚያካፍሏቸው ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ይወስዳሉ። 19 የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥ 20 ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላምያል፥ 21 ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥ 22 ከዳን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዮቅሊ ልጅ ባቂ፥ 23 ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አንሄል፥ 24 ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሳፍጣን ልጅ ቃሙሔል፥ 25 ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የበርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥ 26 ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጥሔል፥ 27 ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አኪሖር፥ 28 ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የአሚሁድ ልጅ ፈዳሄል። 29 እግዚአብሔር በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን ይከፍሉ ዘንድ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።” |