ዘኍል 30 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ብፅዐት የተሰጠ ሥርዐት 1 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ነገራቸው፥ “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። 2 ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም መሐላን ቢምል፤ ራሱንም ቢለይ፥ ቃሉን አያርክስ፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ። 3 ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባቷ ቤት ሳለች በብላቴንነቷ ጊዜ ራስዋን ብትለይ፥ 4 አባቷም ስእለቷንና ራስዋን የለየችበትን ቢሰማ፥ አባቷም ዝም ቢላት፥ ስእለቷ ሁሉ ይጸናል፤ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 5 አባቷ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለቷ፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባቷ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል። 6 “ባል ያገባች ብትሆን፥ በአንደበቷም እንደ ተናገረች ስለ ራስዋ የተሳለችው ስእለት በራስዋ ላይ ቢሆን፥ 7 ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለቷ፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናሉ። 8 ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለቷና ራስዋን ያሰረችበት መሐላ አይጸኑም፤ ባልዋ ከልክሎአታልና፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል። 9 “ባልዋ የሞተባት ወይም የተፋታች ግን ስእለቷና ራስዋን ያሰረችበት መሐላ ይጸኑባታል። 10 ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ 11 ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት፥ ባይከለክላትም፥ ስእለቷ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 12 ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ስእለቷን ቢከለክላት፥ ስለ ስእለቷ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ ከአፍዋ የወጣው ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከልክሏታል፤ እግዚአብሔርም ያነጻታል። 13 “ስእለቷን ሁሉ፥ ነፍስዋንም የሚያዋርደውን የመሐላ ማሰሪያ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፤ ወይም ባልዋ ይከለክለዋል። 14 ነገር ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለቷን ሁሉ፥ በእርስዋም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ ያጸናዋል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል። 15 ከሰማው በኋላ ግን ቢከለክላት ኀጢአቱን ይሸከማል።” 16 እርስዋ በብላቴንነቷ ጊዜ በአባቷ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው ሥርዐት ይህ ነው። |