ዘኍል 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ጥያቄ 1 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገን ፥ የምናሴ ልጅ፥ የማኪር ልጅ፥ የገለአድ ልጅ፥ የኦፌር ልጅ፥ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች መጡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስሞች መሐላ፥ ኑኃ፥ ሄግላ፥ ሚልካ፥ ቴርሳ ነበሩ። 2 በምስክሩም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር፥ በአለቆቹም፥ በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፦ 3 “አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኀጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም። 4 ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? 5 በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን።” ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ። 6 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 7 “የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ ስጥ። 8 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ሰው ቢሞት፥ ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱን ለሴቶች ልጆቹ ትሰጣላችሁ፤ 9 ሴት ልጅም ባትኖረው፥ ርስቱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ፤ 10 ወንድሞችም ባይኖሩት፥ ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ፤ 11 የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ትሰጣላችሁ፤ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዐትና ፍርድ ይሁን።” ኢያሱ በሙሴ ምትክ እንደ ተመረጠ ( ዘዳ. 31፥1-8 ) 12 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደዚህ በናባው አሻገር ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለእስራኤልም ልጆች ይገዙአት ዘንድ እኔ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እያት፤ 13 ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ እንደ ተጨመረ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትጨመራለህ። 14 እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አላከበራችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የክርክር ውኃ ነው።” 15 ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 16 “የሥጋና የነፍስ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የሚሆነውን ሰው ይሹም፤ 17 በፊታቸው የሚወጣውንና የሚገባውን፥ የሚያስወጣቸውንና፥ የሚያስገባቸውንም፥ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን።” 18 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “መንፈስ ቅዱስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ 19 በካህኑም በአልዓዛር ፊት አቁመው፤ በማኅበሩም ፊት እዘዘው፤ ስለ እርሱም በፊታቸው እዘዝ። 20 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ ስጠው። 21 በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፤ በቃሉም ይግቡ።” 22 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንደ አዘዘው፥ እጁን በላዩ ጫነበትና፥ ሾመው፤ አዘዘውም። |