ዘኍል 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሁለተኛው የእስራኤል ሕዝብ ቈጠራ 1 እንዲህም ሆነ፦ መቅሠፍቱ ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2 “ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጣውን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ቍጠሩ።” 3 ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብለው ነገሩአቸው፦ 4 “እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ከሃያ ዓመት ጀምሮ፥ ከዚያም በላይ ያለውን ሕዝብ ቍጠሩ።” ከግብፅ ምድር የወጡ የእስራኤልም ልጆች እነዚህ ናቸው። 5 የእስራኤል በኵር ሮቤል፤ የሮቤል ልጆች፤ ከሄኖኅ የሄኖኃውያን ወገን፤ ከፈሉስ የፈሉሳውያን ወገን። 6 ከአስሮን የአስሮናውያን ወገን፤ ከከርሚ የከርማውያን ወገን። 7 እነዚህ የሮቤላውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 8 የፈሉስም ልጆች፤ ኤልያብ። 9 የኤልያብም ልጆች፥ ናሙኤል፥ ዳታን፥ አቤሮን፤ እነዚህም ከማኅበሩ የተመረጡ ነበሩ፤ ከቆሬ ወገን ጋር በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን ተጣሉ፤ 10 ማኅበሩም በሞቱ ጊዜ ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ በዚያም ጊዜ እሳቲቱ ሁለት መቶ አምሳውን ሰዎች አቃጠለቻቸው፤ እነርሱም ለምልክት ሆኑ። 11 የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም። 12 የስምዖንም ልጆች በየወገናቸው፤ ከናሙሄል የናሙሄላውያን ወገን፥ ከኢያሚን የኢያሚናውያን ልጆች ወገን፥ ከያክን የያክናውያን ልጆች ወገን፥ 13 ከዛራ የዛራውያን ልጆች ወገን፥ ከሳውኡል የሳውኡላውያን ወገን። 14 እነዚህ የስምዖናውያን ወገኖች ናቸው፤ ቍጥራቸውም ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 15 የይሁዳ ልጆች ኤርና አውናን፥ ሴሎምና ፋሬስ ዛራም፤ ዔርና አውናንም በከነዓን ምድር ሞቱ። 16 የይሁዳም ልጆች በየወገናቸው፤ ከሴሎም የሴሎማውያን ወገን፥ ከፋሬስ የፋሬሳውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን። 17 የፋሬስም ልጆች፤ ከኤስሮም የኤስሮማውያን ወገን፥ ከያሙሔል የያሙሔላውያን ወገን። 18 እነዚህ የይሁዳ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 19 የይሳኮር ልጆች በየወገናቸው፤ ከቶላ የቶላውያን ወገን፥ ከፉሓ የፉሓውያን ወገን፤ 20 ከያሱብ የያሱባውያን ወገን፥ ከሥምራ የሥምራውያን ወገን። 21 እነዚህ የይሳኮር ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 22 የዛብሎን ወገኖች በየወገናቸው፥ ከሳሬድ የሳሬዳውያን ወገን፥ ከኤሎኒ የኤሎኒያውያን ወገን፥ ከያሕልኤል የያሕልኤላውያን ወገን። 23 እነዚህ የዛብሎን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 24 የጋድ ልጆች በየወገናቸው፤ ከሳፎን የሳፎናውያን ወገን፥ ከሐጊ የሐጋውያን ወገን፥ ከሱኒ የሱኒያውያን ወገን፤ 25 ከኤዜን የኤዜናውያን ወገን፥ ከሳድፍ የሳዳፋውያን ወገን፤ 26 ከአሮሐድ የአሮሐዳውያን ወገን፥ ከአሩሔል የአሩሔላውያን ወገን። 27 እነዚህ የጋድ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አራት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 28 የአሴር ልጆች በየወገናቸው፤ ከኢያምን የኢያምናውያን ወገን፥ ከኢያሱ የኢያሱያውያን ወገን፥ ከበርያ የበርያውያን ወገን። 29 ከኮቤር ልጆች፤ ከከቤር የከቤራውያን ወገን፥ ከሜልክያል የሜልክያላውያን ወገን። 30 የአሴርም የሴት ልጁ ስም ሳራ ነበረ። 31 እነዚህ የአሴር ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 32 የዮሴፍ ልጆች በየወገናቸው፤ ምናሴና ኤፍሬም። 33 የምናሴ ልጆች፤ ከማኪር የማኪራውያን ወገን፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ ከገለዓድ የገለዓዳውያን ወገን። 34 የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከአክያዝር የአክያዝራውያን ወገን፥ ከኬሌግ የኬሌጋውያን ወገን፥ 35 ከኢሳርያል የኢሳርያላውያን ወገን፥ ከሴኬም የሴኬማውያን ወገን፥ 36 ከሲማኤር የሲማኤራውያን ወገን፥ ከኦፌር የኦፌራውያን ወገን። 37 የኦፌርም ልጅ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዓድም የሴቶች ልጆቹ ስም መሐላ፥ ኑኃ፥ ሄግላ፥ ሚልካ፥ ቴርሳ ነበረ። 38 እነዚህም የምናሴ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 39 በየወገናቸው የኤፍሬም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሱቱላ የሱቱላውያን ወገን ከጣናህ የጣናሃውያን ወገን። 40 እነዚህ የሱቱላ ልጆች ናቸው፤ ከዔዴን የዔዴናውያን ወገን። 41 እነዚህ የኤፍሬም ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው። 42 የብንያም ልጆች በየወገናቸው፤ ከበዓሌ የበዓላውያን ወገን፥ ከአሲቤር የአሲቤራውያን ወገን፥ ከአኪራን የአኪራናውያን ወገን፥ 43 ከሶፋን የሶፋናውያን ወገን፥ 44 የበዓሌም ልጆች አዴርና ኖሐማን፤ ከአዴር የአዴራውያን ወገን፥ ከኖሐማን የኖሐማናውያን ወገን። 45 በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 46 በየወገናቸው የዳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሰምዒ፥ የሰምዒያውያን ወገን፤ በየወገናቸው የዳን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 47 የሰምዒያውያን ወገኖች ሁሉ ቍጥራቸው ስድሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 48 የንፍታሌም ልጆች በየወገናቸው፤ ከአሴሔል የአሴሔላውያን ወገን፥ ከጎሄኒ የጎሄናውያን ወገን፥ 49 ከየሴር የየሴራውያን ወገን፥ ከሴሌም የሴሌማውያን ወገን። 50 በየወገናቸው የንፍታሌም ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 51 ከእስራኤል ልጆች የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 52 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 53 “ለእነዚህ በየስማቸው ቍጥር ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፈላለች። 54 ለብዙዎቹ ብዙ ርስትን ትሰጣቸዋለህ፤ ለጥቂቶችም ጥቂት ርስትን ትሰጣቸዋለህ። ለእያንዳንዳቸው እንደ ቍጥራቸው መጠን ርስታቸውን ትሰጣቸዋለህ። 55 ነገር ግን ምድሪቱ በየስማቸው በዕጣ ትከፋፈላለች፤ እንደ አባቶቻቸው ነገድ ይወርሳሉ። 56 በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸውን በዕጣ ትከፍላለህ። 57 የሌዊ ልጆች በየወገናቸው የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ወገን፥ ከቀዓት የቀዓታውያን ወገን፥ ከሜራሪ የሜራራውያን ወገን። 58 እነዚህ የሌዊ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ የሎቢኒ ወገን፥ የኬብሮን ወገን፥ የሞሓሊ ወገን፥ የሐሙሲ ወገን፥ 59 የቆሬ ወገን፥ የቀዓት ወገን። ቀዓትም እንበረምን ወለደ። በግብፅ ሀገር እነዚህን ሌዋውያንን የወለደቻቸው የሌዊ ልጅ የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ። ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት። 60 ለአሮንም ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛርና ኢታምር ተወለዱለት። 61 በሲና በረሃ በእግዚአብሔር ፊት ከሌላ እሳት ባቀረቡ ጊዜ ናዳብና አብዩድ ሞቱ። 62 ከአንድ ወርም ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉ ወንዶች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩ ሃያ ሦስት ሺህ ነበሩ። ከእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አልተሰጣቸውምና ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 63 በሞዓብ ሜዳ ላይ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ሲቈጥሩ፥ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር የቈጠሩአቸው የእስራኤል ልጆች እነዚህ ናቸው። 64 ነገር ግን ሙሴና ካህኑ አሮን በሲና ምድረ በዳ የእስራኤልን ልጆች በቈጠሩአቸው ጊዜ ከነበሩት ከእነዚያ መካከል አንድም ሰው አልነበረም። 65 እግዚአብሔር ስለ እነርሱ፥ “በእውነት በምድረ በዳ ይሞታሉ” ብሎ ተናግሮአልና። ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ፥ ከነዌም ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእነርሱ አንድ ሰው ስንኳ አልቀረም። |