ዘኍል 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሞዐባውያን እስራኤላውያንን በፌጎር እንደ አሳቱ 1 እስራኤልም በሰጢን አደሩ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር አመነዘሩ፤ ረከሱም። 2 ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም መሥዋዕታቸውን በሉ፤ ለአምላኮቻቸውም ሰገዱ። 3 እስራኤልም ለብዔል ፌጎር ራሳቸውን ለዩ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ፈጽሞ ተቈጣ። 4 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላፈረሱ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐይ ፊት ቅጣቸው። የእግዚአብሔርም ቍጣ ከእስራኤል ይርቃል።” 5 ሙሴም የእስራኤልን ሕዝቦች፥ “እናንተ እያንዳንዳችሁ ብዔል ፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ” አላቸው። 6 እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ወንድሙን ወደ ምድያማዊት ሴት ወሰደው፤ እነርሱም በምስክሩ ድንኳን ዳጃፍ ያለቅሱ ነበር። 7 የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ። 8 ያንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። ሁለቱንም እስራኤላዊውን ሰውና ምድያማዊቱን ሴት ሆዳቸውን ወጋቸው፤ ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተወገደ። 9 በመቅሠፍቱም የሞቱት ሃያ አራት ሺህ ነበሩ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11 “የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። 12 ስለዚህ አልሁ፦ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ። 13 ለአምላኩ ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና፥ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም የክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።” 14 ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። 15 የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም የምድያም አባቶች ወገን የሚሆን የሳሞት ወገን አለቃ ነበረ። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ 17 ምድያማውያንን አስጨንቋቸው፤ ግደሉአቸውም። 18 ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና።” |