ዘኍል 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ወደ ከነዓን የተላኩ ጕበኞች ( ዘዳ. 1፥19-33 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ይገዙአት ዘንድ እኔ ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከነዓንን ምድር የሚሰልሉ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ቤት ከእያንዳንዱ ነገድ ሁሉ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ አንድ ሰው ትልካላችሁ።” 3 ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ። 4 ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዝኩር ልጅ ሰሙኤል፤ 5 ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ ፤ 6 ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ 7 ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ኢጋል፤ 8 ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤ 9 ከብንያም ነገድ የራፋ ልጅ ፈልጢ፤ 10 ከዛብሎን ነገድ የሶዲ ልጅ ጉዲኤል፤ 11 ከዮሴፍ ነገድ ከምናሴ ልጆች የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ 12 ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚሄል፤ 13 ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሳቱር፤ 14 ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤ 15 ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። 16 ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስሞች እነዚህ ናቸው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው። 17 ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፤ አላቸውም፥ “ከዚህ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ፥ ወደ ተራሮችም ውጡ። 18 ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ 19 የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ቅጥር ያላቸው ወይም የሌላቸው እንደ ሆኑ፥ 20 ምድሪቱም ለም ወይም ጠፍ፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች አይታችሁ፥ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤” ወራቱም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ነበረ። 21 ወጡም፤ ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በኤማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ። 22 ወደ ምድረ በዳም ወጡ፤ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ዘሮች አኪማን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ ከተማ በፊት ሰባት ዓመታት ተሠርታ ነበር። 23 ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆም መጡ፤ አዩኣትም፤ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፤ በመሎጊያም ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። 24 የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የወይን ዘለላ ሸለቆ ብለው ጠሩት። የጕበኞች ዘገባ አቀራረብ 25 ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ከዚያ ተመለሱ። 26 ገሥግሠውም በቃዴስ ፋራን ምድረ በዳ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27 እንዲህም ብለው ነገሩት፥ “ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፤ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፤ ፍሬዋም ይህ ነው። 28 ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኀያላን ናቸው፤ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ፥ እጅግም የጸኑ ታላላቅ ናቸው። 29 ደግሞም በዚያ የዔናቅን ዘሮች አየን፤ በአዜብ በኩል ዐማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮችዋም ኬጤዎናዊውና ኤዌዎናዊውም፥ ኢያቡሴዎናዊው፥ አሞሬዎናዊውም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊውም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ተቀምጦአል።” 30 ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፥ “አይደለም! ማሸነፍን እንችላለንና እንውጣ፤ እንውረሳት” አለ። 31 ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን ፥ “በኀይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም” አሉ። 32 ስለ ሰለሉአትም ምድር ለእስራኤል ልጆች እያወሩ፥ “እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው፤ 33 በዚያም ግዙፋን የሆኑትን አየን፤ እኛም በእነርሱ ፊት እንደ አንበጣዎች ሆን፤ እንዲሁም በፊታቸው ነበርን፤” እያሉ የሰለሉአትን ምድር ለእስራኤል ልጆች አስፈሪ አደረጓት። |