ነህምያ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ነህምያ ጠላቶቹን እንደ ተቋቋመ 1 ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ተበሳጨም፤ በአይሁድም ሳቀባቸው። 2 በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት፥ “ከተማቸውን የሚሠሩ እነዚህ ደካሞች አይሁድ ኀይላቸው ምንድን ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን?” ብሎ ተናገረ። 3 አሞናዊውም ጦቢያ ወደ እርሱ ቀርቦ፥ “በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢወጣበት ያፈርሰዋል” አለ። 4 አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ ሀገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው። 5 በደላቸውንም አትክደን፤ ኀጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቈጥተውሃልና። 6 ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ ሕዝቡ ከልብ ይሠራ ነበርና። 7 ሰንባላጥና ጦብያም፥ ዓረባውያንም፥ አሞናውያንም፥ አዛጦናውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። 8 መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያፈርሷት ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተሰበሰቡ። 9 እኛም ወደ አምላካችን ጸለይን፤ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎችን በሌሊትና በቀን አደረግን። 10 ይሁዳም፥ “የተሸካሚዎች ኀይል ደከመ፤ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ። 11 ጠላቶቻችንም፥ “ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ፥ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁም፤ አያዩም” አሉ። 12 በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው፥ “ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው ዐሥር ጊዜ ነገሩን።” 13 ከቅጥሩም በስተኋላ በኩል ባለው በታችኛው ክፍል በሰዋራ ስፍራ ሰይፋቸውንና ጦራቸውን፥ ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው፤ 14 አይችም ተነሣሁ፤ ታላላቆቹንና ሹሞቹንም፥ የቀሩትንም ሕዝብ፥ “አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን አምላካችንን አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁም፥ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ስለ ሚስቶቻችሁም፥ ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ” አልኋቸው። 15 ጠላቶቻችንም እንደ ዐወቅንባቸው፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን። 16 ከዚያም ቀን ጀምሮ እኩሌቶቹ ብላቴኖች ሥራ ይሠሩ ነበር፤ እኩሌቶቹም ጋሻና ጦር፥ ቀስትና ጥሩርም ይዘው በፊትና በኋላ ይጠብቁ ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። 17 ቅጥሩንም የሚሠሩትና ሸክም ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፤ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። 18 አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ። 19 ታላላቆቹንና ሹሞቹን፥ የቀሩትንም ሕዝብ፥ “ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፤ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፤ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤ 20 የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል” አልኋቸው። 21 ሥራውንም እንሠራ ነበር፤ ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኩሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር። 22 ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን፥ “ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፤ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፤ በቀንም ሥሩ” አልኋቸው። 23 እኔና ወንድሞችም፥ ብላቴኖችም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር። ወደ ውኃም ስንሄድ መሣሪያችንን እንደታጠቅን እንሄድ ነበር። |