ነህምያ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በንጉሡ በአርተሰስታ በሃያኛው ዓመተ መንግሥት በኔሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ ነበር፤ ጠጁንም አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። በፊቱም ሌላ ሰው አልነበረም። 2 ንጉሡም፥ “ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኀዘን ነው እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ። 3 ንጉሡንም፥ “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር፤ የአባቶች መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አያዝን?” አልሁት። 4 ንጉሡም፥ “ምን ትለምነኛለህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። 5 ንጉሡንም፥ “ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶች መቃብር ከተማ ስደደኝ” አልሁት። 6 ንግሥቲቱም፦ በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ፥ “መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ጊዜውን ነገርሁት፤ እርሱም አሰናበተኝ። 7 ንጉሡንም፥ “ንጉሥ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ ሀገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይስጠኝ፤ 8 በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ” አልሁት። ንጉሡም ሁሉን ሰጠኝ። የከበረች የአምላኬ እጅ ከእኔ ጋር ነበረችና። 9 በወንዙም ማዶ ወዳሉት ሀገረ ገዦች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው። ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ልኮ ነበር። 10 ሖሮናዊውም ሰንባላጥና አገልጋዩ አሞናዊው ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ። 11 ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥሁ። 12 በሌሊትም ተነሣሁ፤ ከእኔም ጋር ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም። 13 በሸለቆውም በር ወጣሁ፤ ወደ በለስም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ። 14 ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡም መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበት የነበረው እንስሳም የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም። 15 በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ በሸለቆውም በር ገባሁ፤ እንዲሁም ተመለስሁ። 16 ጠባቆች ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹሞቹም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች እስከዚያ ጊዜ ገና አልተናገርሁም ነበር። 17 እኔም፥ “እኛ ያለንበትን ጕስቍልና፥ ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ። አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” አልኋቸው። 18 የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። “ተነሡ እንሥራ” አልኋቸው። እጆቻቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ። 19 ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ አገልጋዩም አሞናዊው ጦቢያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፤ ቀላል አድርገውንም ወደ እኛ መጡና፥ “ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድን ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን?” አሉ። 20 እኔም መልሼ፥ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ንጹሓን ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ዕድል ፋንታና መብት፥ መታሰቢያም የላችሁም” አልኋቸው። |