ዘሌዋውያን 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኀጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሳያውቅ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ 3 የተቀባውም ሊቀ ካህናት በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኀጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኀጢአቱ ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኀጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። 4 ወይፈኑንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። 5 ተቀብቶ የተሾመው ካህን ከወይፈኑ ደም በእጁ ወስዶ ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣዋል፤ 6 ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 7 ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የወይፈኑንም ደም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 8 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 9 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ 10 ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል፤ ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቀርበዋል። 11 የወይፈኑን ቍርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፤ 12 ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዱታል፤ በዕንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥሉታል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። 13 “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከማኅበሩ ዐይን ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፤ 14 ከዚህም በኋላ፥ የሠሩት ኀጢአት ቢታወቃቸውና ንስሓ ቢገቡ ማኅበሩ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን ፊት ያመጡታል። 15 የማኅበሩም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርዱታል። 16 የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣል፤ 17 ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 18 በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 19 ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል። 20 እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንደ አደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ኀጢአታቸውን ያስተሰርያል፤ ኀጢአቸውም ይሰረይላቸዋል። 21 ወይፈኑንም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስዱታል፤ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠሉ ያቃጥሉታል፤ የማኅበሩ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። 22 “መኰንንም ኀጢአትን ቢሠራ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ እንዲህም ቢበድል፥ 23 የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥ ከፍየሎች ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርባል፤ 24 በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። 25 ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 26 ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ኀጢአቱን ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 27 “ከሀገሩም ሕዝብ አንድ ሰው ኀጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ 28 ለእርሱም የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥ ስለ ሠራው ኀጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። 29 እጁንም በኀጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት እንስሳትን በሚያርዱበት ስፍራ የኀጢአት መሥዋዕት ፍየልዋን ያርዳታል። 30 ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 31 ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል። 32 “ስለ ኀጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። 33 እጁንም በኀጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኀጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። 34 ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 35 ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው የበግ ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ሁሉ ይወስዳሉ፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል። |