ዘሌዋውያን 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የደኅንነት መሥዋዕት 1 “ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ቍርባን የደኅንነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከላሞች መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 2 እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፤ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በሚቃጠለው መሥዋዕት፥ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 3 ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርገው ያቀርባሉ፤ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 4 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ያመጣሉ። 5 የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በዕንጨቱ ላይ ያቀርቡታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ነው። 6 “ለእግዚአብሔርም ለደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቍርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል። 7 ለቍርባኑ የበግ ጠቦትን ቢያቀርብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 8 እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ያርደዋል፤ ካህናቱም የአሮን ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 9 ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ሙሉ ላቱን፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 10 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑም አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 11 ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ በጎ መዓዛ ያለው ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 12 “ቍርባኑም ፍየል ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 13 እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፤ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍም ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 14 ከእርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርበዋል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 15 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 16 ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ስቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው። 17 ስብና ደም እንዳትበሉ በምትኖሩበት ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው።” |