ዘሌዋውያን 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእህል ቍርባን 1 “ማናቸውም ሰው ቍርባን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲሆን ቢያቀርብ፥ ቍርባኑ ከመልካም ስንዴ ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስስበታል፤ ነጭ ዕጣንም ይጨምርበታል፤ ይህም መሥዋዕት ነው። 2 ወደ ካህኑ ወደ አሮን ልጆች ያመጣዋል፤ ከመልካም ስንዴ ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ነጩንም ዕጣን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 3 ከመሥዋዕቱም የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር መሥዋዕት የተረፈ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 4 “በእቶን የተጋገረውን ቍርባን ስታቀርብ፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ስንዴ ዱቄት፥ የቂጣ እንጎቻ ወይም በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን። 5 ቍርባንህም በምጣድ የተጋገረ ቍርባን ቢሆን፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ስንዴ ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6 ቈርሰህም ዘይት ታፈስስበታለህ፤ የእግዚአብሔር መሥዋዕት ነው። 7 ቍርባንህም በመቀቀያ የበሰለ ቍርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ስንዴ ዱቄት የተደረገ ይሁን። 8 ከዚህም ያደረግኸውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ታመጣለህ፤ ወደ ካህኑም ታቀርበዋለህ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል። 9 ካህኑም ከቍርባኑ መታሰቢያውን ይወስዳል፤ በመሠዊያውም ላይ ይጨምረዋል። ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው የሚቃጠል ቍርባን ነው። 10 ከመሥዋዕቱም የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር መሥዋዕት የተረፈ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 11 “ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት፤ እርሾ ያለበት ነገር፥ ማርም ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡምና። 12 እነዚህንም ዐሥራት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ለበጎ መዓዛ በመሠዊያው ላይ አይቀርቡም። 13 የምታቀርቡት ቍርባን ሁሉ በጨው ይጣፈጣል፤ የአምላክህም ቃል ኪዳን ጨው ከቍርባንህ አይጕደል፤ በቍርባናችሁ ሁሉ ላይ ጨው ትጨምራላችሁ። 14 “ከመጀመሪያው እህልህ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ብታቀርብ በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸት ታቀርባለህ። 15 ዘይትም ታፈስስበታለህ፤ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። 16 ካህኑም ከተፈተገው እህል፥ ከዘይቱም ወስዶ ከዕጣኑ ጋር መታሰቢያውን ያቀርባል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። |