Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዮዲት ጸሎት 1 ዮዲት ግን በግንባሯ ተደፍታ በምድር ላይ ወደቀች፤ በራሷም ላይ ትቢያ ነሰነሰች፤ የምትለብሰውንም ማቅ አሳየች፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠርክ ዕጣን በሚቀርብበት ጊዜ ዮዲት በታላቅ ቃል ወደ እግዚአብሔር ጮኸች፤ እንዲህም አለች፦ 2 “በማኅፀን ያለ ጽንስን ያጠፉ፥ ድንግልንም ያጐሰቈሉ፥ ልብሷንም የገፈፉ፥ በከተማም በአራቱ ማዕዘን ለመገዳደር ማኅፀንን ያሳደፉ ጠላቶችን ይበቀል ዘንድ በእጁ ሰይፍን የሰጠኸው የአባቴ የስምዖን አምላክ ሆይ፥ አንተ እንዲህ አይደለም አልህ፤ እነርሱ ግን አደረጉት። 3 ስለዚህም አለቆቻቸውን ለመገደል አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ መኝታቸውም በተገደሉት ባሮች ደም ተነከረ፤ ባሮችን ከጌቶቻቸው ጋር፥ ጌቶችንም በዙፋኖቻቸው ላይ ገደልሃቸው። 4 ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ተማረኩ፤ በአንተ ዘንድ የተወደዱ፥ ለአምላክነትህም የቀኑ፥ የረከሰ ደማቸውንም የተጸየፉ፥ ትረዳቸውም ዘንድ የለመኑ የልጆችን ምርኮ ሁሉ ተካፈሉ፤ አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እኔን መበለቲቱን ስማኝ። 5 ከዚህ አስቀድሞና ከዚያም በኋላ የሆነውን አንተ አድርገሃልና የዛሬውንና የሚመጣውንም ታውቀዋለህ፤ አንተም በምታውቀው ሆነ። 6 ምክርህ የቀና ነው፤ ሥርዐትህ የተዘጋጀ ነውና፥ ፍርድህንም አስቀድመህ ባወቅህ ፈርደሃልና እነሆ፥ መጣን ይሉሃል፤ 7 “እነሆ፥ የአሦር ሰዎች ከሠራዊታቸው ጋር በዝተዋልና፥ በፈረሶቻቸውም ላይ ከፍ ከፍ ብለዋልና፥ በፈረስም የተቀመጡ ሰዎች በኀይላቸው ታምነዋልና፥ አርበኞችም በጽናታቸው፥ በቀስታቸውና በጦራቸው፥ በምድር ነጎዳቸውም ታምነዋልና አንተ አርበኞችን የምታጠፋ አምላክ እንደ ሆንህ አላወቁህምና ስምህም አሸናፊ እንደ ሆነ አልተገነዘቡም። 8 አንተ ከሠራዊታቸው ጋር በከሃሊነትህ አጥፋቸው፤ ቤተ መቅደስን ያጐሰቍሉ ዘንድ፥ የስምህ ጌትነት ማደሪያ የሆነች ደብተራ ኦሪትንም ያሳድፉ ዘንድ መክረዋልና፥ በብረትም የመሠዊያህን ቀንዶች አፍርሰዋልና በቍጣህ ኀይላቸውን አጥፋ። 9 ትዕቢታቸውን ተመልከት፤ በራሳቸውም ላይ ቍጣህን አምጣ። እንደ አሰብሁት እፈጽም ዘንድ በእኔ በመበለቲቱ እጅ ኀይልን አድርግ። 10 በአንደበቴ ጥበብ ሎሌውን ከጌታው፥ ጌታውንም ከሎሌው ጋር ግደል። ግርማቸውን በእኔ በሴቲቱ እጅ አጥፋ። 11 ብርታትህ በብዙዎች አይደለምና፥ ኀይልህም በኀያላን ሰዎች አይደለምና፤ ነገር ግን አንተ የትሑታን አምላክ ነህ፤ የጥቂቶች ረዳት ነህ፤ የበሽተኞችም ፈዋሽ አንተ ነህ፤ ለጠፉትም ጠባቂያቸው አንተ ነህ፤ ተስፋ የቈረጡ ሰዎችንም የምታድናቸው አንተ ነህ። 12 አወን አቤቱ የአባቴ አምላክ፥ የእስራኤልም የርስታቸው አምላክ፥ የሰማይና የምድር አምላክ፥ ውኃውን የፈጠርህ፥ የፍጥረታት ሁሉ ንጉሥ አንተ ጸሎቴን ስማ። 13 የቃሌንም ጥበብ በሕግህና በቤተ መቅደስህ በደብረ ጽዮንና በልጆችህ ንብረት ቤት ላይ ክፉ ነገርን የመከሩ ጠላቶችን እንዲያቈስላቸውና እንዲያጠፋቸው አድርግ። 14 የብርታትና የኀይል ሁሉ አምላክ አንተ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ፥ የእስራኤልንም ወገን ከአንተ በቀር ሌላ የሚያጸናቸው እንደ ሌለ ለሕዝቡና ለአሕዛቡ ሁሉ እንዲያውቁት አድርግ።” |