Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በምዕራብ በኩል በሚገኙ ሕዝቦች የተደረገ ጦርነት 1 በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት በጨረቃ አቈጣጠር በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን እንደ ተናገረው ሀገሩን ሁሉ ይበቀል ዘንድ በአሦር ንጉሥ በናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ምክር ተመከረ። 2 ሹሞቹንና አለቆቹን ሁሉ ጠርቶ ከእነርሱ ጋር የምክሩን ምሥጢር ተነጋገረ፤ በሀገሩ ሁሉ ክፉ ነገርን ተናገረ። 3 በአንደበቱ የተናገረውን ትእዛዝ ያልተቀበሉትን ሰዎች ሁሉ ያጠፋቸው ዘንድ ምክር ጨረሱ። 4 ከዚህም በኋላ ምክሩን በጨረሱ ጊዜ የአሦር ንጉሥ ናቡከደነፆር ከእርሱ በታች ያለ ቢትወደዱ ሆሎፎርኒስን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ 5 “የአገሩ ሁሉ ጌታ ገናናው ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ መቶ ሃያ ሺህ በኀይላቸው የታመኑ እግረኞች ሰዎችን መቶ ሃያ ሺህ ፈረሰኞችንም ከፈረሶቻቸው ጋራ ካንተ ጋራ ይዘህ እነሆ በፊቴ ትወጣለህ። 6 በአንደበቴ ለተናገርሁት ነገር መታዘዝን እንቢ ብለዋልና በምዕራብ በኩል ወዳለች ሀገር ትወጣለህ። 7 በእነርሱ ተቈጥቼ እወጣለሁና፥ ምድርንም በሠራዊቴ እግር እሸፍናታለሁና፥ ገንዘባቸውንም እዘርፋቸዋለሁ፥ እበረብራቸዋለሁምና ውኃውንና ሀገሩን ያዘጋጁልኝ ዘንድ ለእነርሱ አዋጅ ትነግራለህ። 8 ቍስለኞቻቸውም በሸለቆውና በፈሳሹ ይመላሉ፤ ወንዙም ሬሳቸውን ተመልቶ ይፈስሳል፤ 9 ምርኳቸውንም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እበትነዋለሁ። 10 አንተ ግን ቀድመህ አውራጃዎቻቸውን ሁሉ ያዝልኝ፤ ራሳቸውን ወዳንተ ቢመልሱ በእነርሱ እስከምፈርድበት ቀን ለእኔ ትጠብቃቸዋለህ። 11 ዐመፀኞችን ታጠፋቸው ዘንድ፤ በሄድህበትም ሁሉ ትዘርፋቸው ዘንድ ዐይንህ አትራራላቸው። 12 እኔ ሕያው ነኝና እንደ ተናገርሁም ይኽን በእጄ አደርግ ዘንድ መንግሥቴ ጽኑዕ ነውና። 13 እንዳዘዝሁህ አድርግ እንጂ አንተም ከእኔ ከጌታህ ቃል አንዲት ስንኳ የምትተወው አይኑር፤ ይህንም ፈጥነህ አድርግ።” የሆሎፎርኒስ ዘመቻ 14 ሆሎፎርኒስም ከጌታው ፊት ወጥቶ ኀያላኑን፥ አዛዦችንና የአሦር ሠራዊት አለቆችን ሁሉ ጠራቸው። 15 ጌታውም እንዳዘዘው መቶ ሃያ ሺህ የተመረጡ እግረኞች አርበኞችንና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ቀስተኞችን ቈጠረ። 16 ፈጽመው ይዋጉ ዘንድ አዘዛቸው። 17 ስንቃቸውንም የሚጭኑባቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ግመሎችንና አህዮችን፥ በቅሎዎችንም፥ ምግብም ሊሆኗቸው ቍጥር የሌላቸው በሬዎችንና በጎችን፥ ፍየሎችንም ወሰደ። 18 ለብዙ ሰዎችና ለሠራዊቱ ሁሉ ከንጉሡ ቤት እጅግ ብዙ የሆነ ብርና ወርቅን ስንቅ አድርጎ ሰጣቸው። 19 እርሱም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ወጣ፤ በፈረሶችና በሠረገላዎች፥ በተመረጡ አርበኞችም በምዕራብ አንጻር ያለ ምድርን ሁሉ ይሸፍን ዘንድ ከንጉሡ አስቀድሞ ዘመተ። 20 ከእነርሱም ጋር አንድ የሆኑ፥ ብዛታቸውም እንደ አንበጣና እንደ ባሕር አሸዋ የሆኑ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወጡ። ከብዛታቸውም የተነሣ ቍጥር የላቸውም። 21 ከነነዌም ወጥተው በበቄጤሊት ሜዳ አንጻር የሦስት ቀን ጎዳና ሄዱ፤ ከላይኛው ቂልቅያ በስተግራ በኩል ባለው ተራራ አጠገብ በበቄጤሊት አንጻር ሰፈሩ። 22 ከዚያም ሆሎፎርኒስ ሠራዊቱን ሁሉ፥ ፈረሰኞችንና እግረኞችንም፥ ሠረገላዎችንም ይዞ ወደ ተራራማው ሀገር ሄደ። 23 ፌድንና ሎድንም ወጋቸው፤ የሬስስን ልጆችን ሁሉ፥ በኤሌዎን ግራ አንጻር ባለ ሜዳ የሚኖሩ የእስማኤልንም ልጆች ማረካቸው። 24 ኤፍራጥስንም ተሻግሮ ወደ መስጴጦምያ ሄደ፤ ወደ ባሕርም እስኪደርስ ድረስ በአርባኒ ወንዞች ላይ ያሉ ታላላቅ ከተሞችን ሁሉ አፈረሰ። 25 የቂልቅያንም አውራጃ ያዘ፤ ጠላቱንም ሁሉ አጠፋ፤ በምዕራብም አንጻር በዐዜብ በኩል እስከ ያፌት አውራጃ ድረስ ሄደ። 26 የምድያምንም ልጆች ሁሉ ከበባቸው፤ ከብታቸውንም ዘረፈ፤ ቤታቸውንም አቃጠለ። 27 በስንዴ አዝመራ ጊዜም በደማስቆ ወዳለ ሜዳ ወርዶ አዝመራቸውን ሁሉ አቃጠለ፤ የላሞቻቸውንና የበጎቻቸውንም መንጋዎች ይዘርፏቸው ዘንድ አዘዘ፤ አምባቸውንም አፈረሰ፤ ልጆቻቸውንም ማረከ፥ ጎልማሶቻቸውንም ሁሉ በጦር ገደለ። 28 ከእነርሱም የተነሣ መፍራትና ድንጋጤ በባሕሩ ዳርቻ በጢሮስና በሲዶና በሚኖሩ፥ በአቂናና በሴይርም፥ በያምኒያም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ወደቀ። በአስቀሎናና በአዛጦንም የሚኖሩ ሰዎች ከርሱ መምጣት የተነሣ ፈጽመው ፈሩ። |