Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዮዲት በሆሎፎርኒስ እንደ ተጋበዘች 1 የብር ዕቃ ወደሚቀመጥበት ድንኳን ያገቧት ዘንድ አዘዘ፤ ለእርሱም ከሚያዘጋጁት ምግብ ይመግቧት ዘንድ፥ እርሱ ከሚጠጣው መጠጥም ያጠጧት ዘንድ አዘዘ። 2 ዮዲትም፥ “ካመጣሁት እህል እመገባለሁ እንጂ በደል እንዳይሆንብኝ ከእርሱ አልመገብም” አለች። 3 ሆሎፎርኒስም፥ “ያመጣሽውስ ቢያልቅብሽ እንደ እርሱ ያለ ከየት አምጥተን እንሰጥሻለን? ከወገኖችሽ ስንኳ ካንቺ ጋር ያለ ሰው የለም” አላት። 4 ዮዲትም፥ “እግዚአብሔር በእኔ ቃል የመከረውን እስኪያደርግ ድረስ እኔ አገልጋይህ የያዝሁትን እንዳልጨርስ ጌታዬ ሕያው ነፍስህን” አለችው። 5 የሆሎፎርኒስም አሽከሮች ወደ ድንኳኑ አገቧት፤ እስከ እኩለ ሌሊትም ድረስ ተኛች። ሌሊቱም ከመንጋቱ በፊት በእኩለ ሌሊት ተነሣች፤ 6 “እኔ አገልጋይህ ለጸሎት እንድወጣ ይፈቅዱልኝ ዘንድ እዘዝልኝ” ብላ ወደ ሆሎፎርኒስ ላከች። 7 ሆሎፎርኒስም እንዳይከለክሏት የሚጠብቁትን ሰዎች አዘዛቸው፤ ከዚህ በኋላም በሰፈር ሦስት ቀን አደረች፤ በየሌሊቱም እየወጣች ወደ ቤጤሌዋ ሸለቆ ትወርድ ነበር፤ ሌሊትም በሰፈሩ ምንጭ ውኃ ትታጠብ ነበር፤ ሌሊትም ወጥታ በምንጩ ውኃ ትጠመቅ ነበር። 8 ከውኃውም በወጣች ጊዜ ስለ ወገኖችዋ ልጆች መነሣት መንገድዋን ያቃናላት ዘንድ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ትጸልይ ነበር። 9 ከዚህም በኋላ ትመለስ ነበር፤ በሰፈርም በንጽሕና ትቀመጥ ነበር፤ ማታ ማታም ትመገብ ነበር። 10 ከዚህም በኋላ በአራተኛዪቱ ቀን ሆሎፎርኒስ ለአሽከሮቹ ለብቻቸው ምሳ አደረገ፤ ሌላ ሰው ማንንም ወደ ምሳው አልጠራም። 11 የገንዘቡ ሁሉ መጋቢ የሆነውን ጃንደረባ ባግዋን፥ “በአንተ ዘንድ ያለች ያችን ዕብራዊት ሴት ወደ እኛ ትመጣ ዘንድ አባብልልኝ፤ ከእኛ ጋር ትብላ፤ ትጠጣም፤ ሄደህም ንገራት። 12 እንዲህ ያለች ሴት አግኝተን ባናነጋግራት ለእኛ ዕፍረታችን ነውና፥ ባንገናኛትም ይስቁብናልና” አለው። 13 ባግዋም ከሆሎፎርኒስ ዘንድ ወጥቶ ወደ እርሷ ገባ፥ “መልከ መልካም የሆንሽ አንቺ ልጄ ሆይ! ወደ ጌታዬ መምጣትን እንቢ አትበዪ፤ በእርሱ ዘንድ ትከብሪያለሽ፤ ከእርሱም ጋራ ወይንን ጠጥተሽ ደስ ይልሻል፤ በናቡከደነፆር ቤት ከሚያገለግሉት ከአሦር ልጆችም እንደ አንዲቱ ትሆኛለሽ” አላት። 14 ዮዲትም አለችው፥ “ጌታዬን እንቢ እለው ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ወገኔስ ማን ነው? የወደድኸውን ሁሉ በፊትህ ፈጥኜ አደርጋለሁ፤ እስክሞትም ድረስ ለእኔ ደስታ ይሆንልኛል፤” 15 ተነሥታም ልብሷን ለበሰች፤ የሴቶችንም ጌጥ ሁሉ ፈጽማ አጌጠች፤ ብላቴናዋም ከእርሷ ጋራ ሄደች፤ ከባግዋ የተቀበለችውን፥ በማደሪያዋ ያነጠፈላትን፥ ምሳም ስትበላ የምትቀመጥበትን ምንጣፏን በሆሎፎርኒስ ፊት በምድር ላይ አነጠፈችላት። 16 ዮዲትም ወደ እርሱ ገብታ ተቀመጠች፤ የሆሎፎርኒስም ልቡናው በእርሷ ታወከ፤ ከእርሷም ጋር ይተኛ ዘንድ ሰውነቱ ፈጽማ ጐመጀች፤ ከአያትም ጀምሮ እርሷን እስከሚያባብልበት ጊዜ ይጠብቃት ነበር። 17 ሆሎፎርኒስም ዮዲትን፥ “ጠጥተሽ ከእኛ ጋር ደስ ይበልሽ” አላት። 18 ዮዲትም፥ “ከተወለድሁ ጀምሮ ከዘመኔ ሁሉ ይልቅ ሕይወቴ ዛሬ ከብራለችና ጌታዬ እጠጣለሁ” አለችው። 19 አገልጋይዋም ያዘጋጀችላትን ተቀብላ በፊቱ በላች፤ ጠጣችም። 20 ሆሎፎርኒስም ስለ እርሷ ደስ አለው፤ ከተወለደም ጀምሮ አንዲት ቀን ስንኳ እንደዚያ ያልጠጣውን ብዙ ወይን አብዝቶ ጠጣ። |